ታህሳስ ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ማክሰኞ በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ በተደረገው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ከመድረክ ይተላለፍ የነበረውን ዝግጅት በምልክት ቋንቋ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች እንዲያስተላልፍ ተመድቦ የነበረው ሰው፤ ያሳይ የነበረው አካላዊ እንቅስቃሴና ምልክት የውሸት እንደነበር መጋለጡን ዓለማቀፍ ብዙሀን መገናኛ እየዘገቡ ነው።
ድርጊቱ የደቡብ አፍሪካን መንግስትና በ ዓለማቀፍ ደረጃም መስማት የተሳናቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ክፉኛ አስቆጥቷል።
ከነ ባራክ ኦባማና ከሌሎች የዓለም መሪዎች ጎን በመቆም ንግግራቸውን በምልክት እንደሚተረጉም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ታምሳንጋ ዲያንቲ በበኩሉ የቀረበበትን ወቀሳ እና ክስ ተከትሎ ፦ “በመድረኩ ላይ ራሴን አላውቅም ነበር።ስለዚህ ምን እንዳልኩና እንደወራሁ አላስታውስም።ልሣሳት የምችልበት፡ዕድል ሰፊ ነው”ብሏል።
“እያስተረጎምኩ እያለሁ ነጫጭ የለበሱ መልዓኮች ከሰማይ ወርደው በመሬት ላይ ሲነጠፉ አየሁ። ከዛ በሁዋላ ራሴን የት እንዳለሁ አላወቅኩትም። ሌላ ዓለም ውስጥ ነበር ያለሁት”ነው ያለው ዲያንቲ-ለቢቢሲ።
ለሥራው የመደበው የ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በበኩሉ ዲያንቲን ቀደም ሲልም ለተመሣሳይ ሥራዎች ብዙ ጊዜ እንደመደበው እና የዚህ ዓይነት ወቀሳ እና ክስ ቀርቦበበት እንደማያውቅ አስተባብሏል።
ይሁንና በማንዴላ መታሰቢያ ላይ ስለተፈጠረው ችግር ኤ.ኤን.ሲ ምንም አስተያዬት ሳይሰጥ ነው ያለፈው።
የደቡብ አፍሪካ የትርጉም ተቋም ግን ዲያንቲ ቀደም ሲልም ተመሣሳይ ጥፋቶች እንደሚሠራ ክሶች ቢቀርቡበትም ኤ.ኤን.ሲ የማስተካከያ እርምጃ ባለመውሰዱ እና አሁንም በዚህ ታላቅ ፕሮግራም ላይ እንዲመደብ በማድረጉ ችግሩ እንደተፈጠረ በመግለጽ የ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን ወቅሷል።
በአሁኑ ጊዜ ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሆነ የደቡብ አፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ምክትል ሚኒስትርን በመጥቀስ ቢቢሲ ዘግቧል።