ታህሳስ ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ሀቅሙ ላላቸው ዜጎች የ40 በ60 እንዲሁም በአዲስ አበባ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ደግሞ የ10 በዘጠና እና የ20 በ80 የቤት ልማት እዶችን ዘርግቷል።
በ10/90 850 ሺ በ 20/80 ደግሞ 350 ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪ ተመዝግቦ እድሉን በመጠባበቅ ላይ ሲሆን ከ12 ሺ በላይ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 40 በ60 በሚባለው ውስጥ ታቅፈዋል።
በመርሀግብሩ ዝግጅት የተሳተፉ የውስጥ ምንጮች እንደገለጹት መንግስት ይህን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ ፈተና ገጥሞታል ።
የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት እቅዱን ለመተግበር 4 ዋና ዋና ችግሮች አጋጥሟል። የመጀመሪያው ችግር በሁሉም ደረጃዎች የተመዘገቡ ሰዎችን ፍላጎት ለማርካት ወደ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ቤቶች መገንባት ይኖርባቸዋል። ይህን ያክል ቤት ለመገንባት ደግሞ ቢያንስ 30 ሺ ሄክታር መሬት ስፋት ያለው ቦታ ያስፈልጋል። አዲስ አበባ ደግሞ ይህን ያክል ሰፊ መሬት ለማግኘት አትችልም።
የፌደራል መንግስቱ ለአዲስ አበባ ታላቅ የማስተር ፕላን በማዘጋጀት እና በማስተር ፕላኑ ውስጥ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የሚባሉትን ሱሉልታ፣ ሰንዳፋና ገላንን በማካተት በቂ የቤት መስሪያ ቦታዎችን ለማፈላለግ እቅድ ነድፎ ቢንቀሳቀስም፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ” ከእንግዲህ መሬት ለአዲስ አበባ መስተዳድር መሬት የምንሰጠው በመቃብራችን ላይ ነው” የሚል አቋም በመውሰዱ እቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል።
በኦሮሚያ ክልል አቋም አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የፌደራሉ መንግስት ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለስልጣናትን በመሰብሰብ እና አንድ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ክልሎች ልኳቸዋል። እነዚህ ባለስልጣኖች ወደ ተለያዩ ክልሎች በመውረድ ክልሎች ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያዘጋጁ ለማግባባት ይሞክራሉ። ክልሎች ፈቃደኛ ሆነው ሲገኙ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዲያስፖራ አባላት ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በክልሎች ግንባታ እንዲያካሂዱ ለማግባባት እንቅስቃሴ ይጀምራሉ።
መንግስት ከዳያስፖራው የሰበሰበውን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የቀረው ምርጫ የዲያስፖራ ቤተ ሰሪዎችን በክልሎች ሄደው እንዲሰሩ ማግባባት መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ። በዘር ላይ የተመሰረተው የፌደራል ስርአት የአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ሄዶ ቤት ለመስራት እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ መንግስትን ለተጨማሪ ራስ ምታት ዳርጎታል።
መንግስትን የገጠመው ሌላው ፈተና የገንዘብ እጥረት ነው። ንግድ ባንክ ለቤቶች ግንባታ የሚሆን 12 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠት የሚኖርበት ሲሆን፣ በቅርቡ የንግድ ባንኩ ፕሬዚዳንት ከጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተገናኙበት ወቅት ባንካቸው ማበደር የሚችለው 6 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልጸውላቸዋል። አቶ ሀይለማርያምም ባንኩ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ብር ማበደር እንዳለበት ትእዛዝ ሰጥተዋል። ባንኩም ለታዋቂዎቹ የመጠጥ አምራች ድርጅቶች ማለትም ለሀይነከንና ዲያጎ የቢራ አምራች ፋብሪካዎች ፈቅዶት የነበረውን የ3 ቢሊዮን ብር የብድር ውል በመሰረዝ፣ ድርጅቶቹ 560 ሚሊዮን ብር ብቻ እንዲበደሩ በማድረግ ቀሪውን ገንዘብ ለዚሁ ፕሮጀክት ለማዋል ተስማምቷል። ባንኩ እስካሁን 8 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ የመንግስትን ጥያቄ ለማሙዋላት ተጨማሪ 2 ቢሊዮን ብር ከየት እንደሚያመጣ ግልጽ አልሆነም።
በሌላ በኩል ደግሞ የቤቶች መስሪያ ዋጋ መጀመሪያ ከታቀደበት መጠን እንዲከለስ ተደርጓል። በመጀመሪያ ለ3 መኝታ ቤት መስሪያ የተመደበው ገንዘብ 385 ሺ የነበረ ሲሆን በተከለሰው አዲስ ዋጋ ግን ይህ ዋጋ በእጥፍ አድጎ 779 ሺ ብር እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ዋጋ በቅርቡ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ አንድ ሚሊዮን እንደሚጠጋ ምንጮች ገልጸዋል። ዲያስፖራው ይህን ገንዘብ ግማሹን በአንድ ጊዜ ቀሪውን ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ እንዲከፍል ይጠበቅበታል። አስገራሚው ነገር ይላሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች፣ መንግስት ከሚሰራው ቤት የተሻለ ጥራት ያለው ቤት በ450 ሺ ብር ማግኘት መቻሉ ነው።
ንግድ ባንክ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሲመዘግብ ቆይቶ በመጨረሻም ምዘገባው እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው የዲያስፖራ አባላት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በብር መክፈል ሲገባቸው በዶላር እንዲከፍሉ መገደዳቸው የአገሪቱን ህግ ከመጻረሩም በላይ ፣ መንግስት ራሱ ለሚያትመው ብር ዋጋ እንዳልሰጠ የሚያመለክትና ለብር ውድቀት ሌላ ምክንያት የሚሆን ነው በሚል ምዝገባው ተቋርጧል።
መንግስት ከዳያስፖራው ገንዘብ በዶላር ለመቀበል የፈለገበት አንዱ ምክንያት ከአባይ ግድብ ጋር የተያያዘ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ዲያስፖራው ለግድቡ ማሰሪያ 1 ቢሊዮን ዶላር ያዋጣል የሚል እቅድ ዘርግተው ነበር። ይሁን እንጅ እስከዛሬ የተሰበሰበው 19 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ያስደነገጣቸው የመንግስት ባለስልጣናት በቤት ግንባታ ስም ለግድቡ ማሰሪያ ተጨማሪ ገንዘብ ለማሰባሰብ ተጨማሪ እቅድ ቢያቅዱም ይህም እቅድ አደጋ ገጥሞታል።
ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ሌላው ችግር የሆነው ተናቦ ለመስራት አለመቻል መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ። ለቤቶች ግንባታ ሃላፊነት በተሰጣቸው ሚኒስትር መኩሪያ ሀይሌ፣ በአዲስ አበባው ከንቲና ድሪባ ኩማ፣ በንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና በውጭ ግንኙነት ሚ/ሩ ቴዎድሮስ አዳህኖም መካከል መናበብ በመጥፋቱ ፕሮጀክቱ ባለበት የቆመ ሲሆን፣በተለይም እያንዳንዱ ባለስልጣን ኢህአዴግን ከመውደቅ ያዳንኩት እኔ ነኝ ለማለት ሁሉም የራሱን እቅድ አውጥቶ ሳይናበብ እየሰራ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ አበባን ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን ለማነጋገር ስልክ ብንደውልላቸውም ሌላ ጊዜ ደውሉ ካሉን በሁዋላ በተለያዩ ጊዜያት ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልም። የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳም ስልክ በደወልንበት ወቅት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ውጭ በመውጣታቸው ልናገኛቸው አልቻልንም። በዚህ ጉዳይ የተሰራውን ዝግጅት በቅርቡ የምናቀርብ መሆናችንን ለመግለጽ እንወዳለን።