ህዳር ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመርካቶ በተለምዶ ጆንያ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትላንት ከቀትር በኃላ የደረሰውን የእሳት አደጋ በወቅቱ ከመቆጣጠር ይልቅ ጉቦ ለማግኘት የእሳት አደጋ ሰራተኞች በድርድር ጊዜ በማጥፋታቸው ንብረታችንን እንድናጣ አድርጎናል ያሉ ነጋዴዎች የአዲስአበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲን ለመክሰስ መወሰናቸውን አስታወቁ፡፡
ከተጎጂ ነጋዴዎች መካከል አንዱ የሆኑት ለአዲስ አበባው ዘጋቢ እንደተናገሩት እሳት አደጋው በግምት ከቀኑ 8፡00 ሰአት ገደማ መነሳቱንና በወቅቱ ለእሳት አደጋ ቢሮው የድረሱልን የስልክ ጥሪ ቢያደርጉም የአደጋ ተከላካይ ሠራተኞቹ በቦታው የተገኙት አንድ ሰዓት ገደማ ዘግይተው ነው፡፡
ከመጡም በኃላ እሳቱን ከማጥፋት ይልቅ ሆን ብለው መዘግየት በመፍጠርና ውሃውን ወደሌላ አቅጣጫ በመርጨት እሳቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢ ነጋዴዎች ሰራተኞቹን በመማጸንና ገንዘብ አዋተው በመስጠታቸው ከአምስት ሰዓታት ቃጠሎ በኃላ በርካታ ንብረት ወድሞ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ኤጀንሲው ግን ለአደጋው መባባስ የቤቶቹ አሰራርና በውስጣቸው ያሉ ተቀጣጣይ ነገሮች ምክንያት መሆናቸውን ትላንት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን መግለጫ አስታውቌል፡፡
ተጎጂዎቹ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈሩት ጥሪት በቀላሉ በቁጥጥር ስር ሊውል በሚችል አደጋ መውደሙ እጅግ እንዳሳዘናቸው በመጥቀስ ኤጀንሲውን ፍ/ቤት ለመገተር ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከንቲባ በቃጠሎ ቦታ ተገኝተው በአደጋው ንብረታቸው የወደመባቸውን ተጎጂዎች አጽናንተዋል።
በአደጋው በ10 ሰዎች ላይ ጉዳት ከመድረሱ በስተቀር በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ የሞት ጉዳት ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም