ህዳር ፲፫(አስራ ሦስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ መስተዳድር ትናንትና ዛሬ በቡራዩ አካባቢ ከ1 ሺ ያላነሱ ቤቶችን ማፍረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ነዋሪዎች እንደሚናገሩት መስተዳድሩ ምንም አይነት መጠለያ ሳያዘጋጅ እና ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ እስከ ሙሉ የቤት እቃዎቻቸው ቤቶቻቸውን በድንገት በማፍረሱ ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀዋል።
አለማየሁ የተባለ አንድ ወጣት የወላጆቹ ቤት ሲፈርስ በማየቱ ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት፣ በህይወቱ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክር ሰዎች ደርሰው አድነውታል። ወጣት አለማየሁ ችግሩ ከሚችለው በላይ ስለሆነበት እራሱን ለማጥፋት እንደወሰነ ለኢሳት ተናግሯል።
መስፍን የተባለ አንድ ወጣት ራሱን ማጥፋቱን መዘገባችን ይታወሳል። በአሁኑ ጊዜ በሳውድ አረቢያ የስደተኞች መመለሻ ካምፕ ውስጥ የምትገኝ ኢትዮጵያዊት፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በምትጠባባቅበት በዚህ ወቅት፣ በዛሬው እለት ቤቷ እንደፈረሰባት የአካባቢው ሰዎች ገልጸዋል። ሁኔታውን ለልጅቷ ለማስረዳት እንደተጨነቁ ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።