ጥቅምት ፳፮(ሃያ ስድስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዢው ፓርቲ መጪውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለማክበር በጅጅጋ ከተማ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ለገዢው ፓርቲ ታማኞች ናቸው የተባሉና ” በተለምዶ ልማታዊ አርቲስትና ጋዜጠኞች እየተባሉ የሚጠሩ ታዋቂ ሰዎች አካባቢውን በመጎብኘት አድናቆታቸውን ሰጥተዋል።
ኢሳት በክልሉ ያለውን ሁኔታ ከዘገበ በሁዋላ የተለያዩ ነዋሪዎች እና ጎብኝዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ክልሉን በቅርቡ አይታ የተመለሰች የመሀል አገር ወጣት፣ ዘመዶቿን ለመጠየቅ መሄዷን ተናግራ፣ እግሩ አካባቢውን እንደረገጠ መውጫዋን ታስብ እንደነበር ተገልጻለች። ጅጅጋ ሱቅ ሄዶ በሰላም መመለስ እንኳን ደስ ያለህ ያሰብላል የምትለው ወጣት፣ ፍተሻው፣ ዘረኝነቱና ዱላው ነዋሪውን እንዳስመረረው ትገልጻለች። ወጣቱዋ በልዩ ሚሊሺያዎች መደብደቡዋን ገልጻለች። ጉራጌውን “አንተ ብርሀኑ ነጋ አይደልህም፣ ኦሮሞውንም ኦነግ እያሉ ወደ እስር ቤት እንደሚወስዱ ምትናገረው ወጣቷ፣ ሀበሻውን ቆሻሻ እስከማለት መድረሳቸውን ትገልጻለች
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ጅጅጋ ውስጥ ነዋሪ ነው። በክልሉ ከመጨውም ጊዜ በላይ ውጥረት መኖሩንና ጫካ የነበሩት ልዩ ሚሊሺያ የሚባሉት ሀይሎች ጠቅልለው መግባታቸውን ይናገራል። የብሄረሰቦች ቀን የሚባለው ፌዝ ነው ሲል ነዋሪው ያጣጥለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች አጥሮቻቸውን ቀለም እንዲቀቡ እየተገደዱ ሲሆን፣ ቀለም መቀባት ያልቻሉት የገንዘብ ቅጣት ይጣልባቸዋል።