ጥቅምት ፳፮(ሃያ ስድስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከወራት በፊት በግብጽ የተቀሰቀሰን አመጽ ተከትሎ በወታደራዊ ሀይሉ ጣልቃ ገብነት ከስልጣን የተወገዱትና በእስር ላይ የሚገኙት መሀመድ ሙርሲ በካይሮ ጉዳያቸውን እንዲያስችል በተሰየመው ፍርድ ቤት ቀርበው የግብጽ ፕሬዳንት መሆናቸውን ተናገሩ።
ሙርሲ፦የተከሰሱበት መንገድ ህገወጥ መሆኑንና እርሳቸው የግብጽ ህጋዊ ፕሬዳንት ሆነው መቀጠል እንዳለባቸው ነው ለዳኞች የተናገሩት።
እንደ ቢቢሲ ሪፖርት ሙርሲና ሌሎች 14 የሙስሊም ብራ ዘር ሁድ ከፍተኛ አመራሮች ባለፈው ኣመት በፕሬዳንቱ ህንፃ ፊት ለፊት የተነሳውን አመጽ ተከትሎ ለተገደሉት ሰዎች ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ህ ብን ለዓመጽ የማነሣሳት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ሙርሲና የፓርቲያቸው አመራሮች ትናንት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ተከሳሾች መልበስ ያለባቸውን ዩኒፎርም ለመልበስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ዳኞቹ ጉዳያቸውን ሳያዩ ወደ ጃንዋሪ አስተላልፈውታል።
ያንን ተከትሎ ፕሬዳንት ሙርሲ አልክሳንደሪያ ወደሚገኘውና “ቡርጂ አል አረብ” ተብሎ ወደሚጠራው እስር ቤት ተወስደዋል።
ሙርሲ በእስር ቤቱ ከተመዘገቡ በሁዋላ ለመለስተኛ የጤና ምርመራ ወደሆስፒታል መወሰዳቸውን የደህንነት ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ተኝተው መታከም አለያም ወደ እስር ቤቱ መመለስ እንዳለባቸው ለማወቅ ገና የምርመራ ውጤቱ እየተጠበቀ ነው ተብሏል።
በምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን የመጡት የሙስሊም ብራዘር ሁዱ መሀመድ ሙርሲ ወደሥልጣን በወጡ በአንደኛ ዓመታቸው የተነሳባቸውን የህዘብ አመጽ ተከትሎ በሠራዊቱ ጣልቃ ገብነት ከከፕሬዘዳንትነታቸው ተነስተው መታሰራቸው ይታወቃል።