ጥቅምት ፳፭(ሃያ አምስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በ ግንባታ ዘርፍ በየጊዜው እየናረ የመጣው የግብአቶች ዋጋ ንረት በተለይ በብድር የሚሰሩ በርካታ ግንባታዎችን እያስተጓጎለ እንደሚገኝ ታውቋል።
ከመንገዶች ባለስልጣን የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው የግንባታ ግብአቶች ዋጋ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ100 እስከ 237 በመቶ የዋጋ ንረት አሳይቶአል፡፡
መረጃው እንደአብነት ከዘረዘራቸው ግብአቶች መካከል ነዳጅ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በሊትር 7.13 ብር የነበረው እ.ኤ.አ በ2013 ወደ 16.91 ብር ወይም 237 በመቶ አሻቅቧል፡፡ ብረት በኪሎ ግራም 18 ብር የነበረው በአሁኑ ወቅት 31.40 ወይም 174 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ሲሚንቶ 167 ብር የነበረው ወደ 230 ብር አሻቅቧል።
ይህ ከፍተኛ የዋጋ ንረት በተለይ በብድር የተያዙ ፕሮጀክቶችን ለተጋነነ ተጨማሪ ወጪ የሚዳርግና የፕሮጀክቶቹም ሒደት በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ አሉታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ ነው ተብሎአል፡፡
ለዚህ ዓይነት ችግር ከተጋለጡ ፕሮጀክቶች መካከል የአዲስአበባ -አዳማ የፍጥነት መንገድ አንዱ ሲሆን የመንገድ ስራው ክፍያው ሲፈጸም የቆየው የዋጋ ንረቱን ማካካሻ ጨምሮ ስለነበር ፣ ቀደም ሲል በተያዘው ገንዘብ ፕሮጀክቱን ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡
ፕሮጀክቱ የግንባታ ግብዐቶች ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት የጨመረ ስለሆነ እስኪጠናቀቅ ድረስ
በውሉ መሰረት ለሚሰላው ዋጋ ማካካሻ ብቻ 251 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ከውሉ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ያህል እንደሚሆን ታውቋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ በጅምር የቀሩት ግንባታዎች አገሪቱን በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠር ብር ኪሳራ ከዳረጉዋት በሁዋላ ትምህርት ሚኒስቴርና ዩኒቨርስቲዎች እርስ በርስ መካሰስ ይዘዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ 3 እና 4 አመታት በፊት መጠናቀቅ ለነበረባቸው ህንጻዎች ትምህርት ሚኒስቴር በቂ ክትትል ለማድረግ ባለመቻሉ ለመዘግየቱ ምክንያት መሆኑን ዩኒቨርስቲው ገልጿል።