ጥቅምት ፳፪(ሃያ ሁለት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ሌተናንት ጄኔራል ሆነው የተሾሙት በሱዳን የሚገኘውን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር በመሆን በጸጥታ መስከበር ስራ ላይ የተሰማራውን የኢትዮጵያ ጦር የሚመሩት ምናልባትም ጀኔራል ሳሞራ የነሱን ሊተኩ ይችላሉ የሚባሉት ሌተናንት ጀኔራል ዮሀንስ ገብረመስቀል ተስፋማርያም በአዲስ አበባ የገነቡዋቸው የንግድ ህንጻዎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዋጋ እንደሚያወጡ ለእርሳቸው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ገልጸዋል።
ጀኔራሉ ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ አዲሱን ሹመታቸውን ከተቀበሉ በሁዋላ የ10 ሺ ዶላር ወርሀዊ ደሞዝ ባለቤት ቢሆኑም ህንጻዎችን የገነቡዋቸው ቀድም ብሎ መሆኑን ገልጸዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ካልዲስ ኮፊ እየተባለ ከሚጠራው ድርጅት ጀርባ የገነቡት ግዙፍ ህንጻ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፣ በዋጋ ደረጃ ከ90 እስከ መቶ ሚሊዮን ብር ያወጣል ተብሎ ይገመታል ብለዋል። ግለሰቡ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎችን ከመኖሪያ ቤታቸው በተጨማሪ ድርጅቶች አሉዋቸው።
ሜ/ጄ ዮሃንስ ገብረመስቀል ተስፋማርያም አብየ የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባረ ጦር ሲመሩ በድክመትና ምግባረ ብሉሽነት ባካባቢው ነዋረዎች ሲወቀሱ ይሰማል::
ጄኔራሉ ከኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። በዘገበው የጀኔራሉን አስተያየት ለማካተት አልተቻለም።
መንግስት በቅርቡ በርካታ ጄኔራሎችን መሾሙ ይታወሳል። አብዛኞቹ ተሹዋሚዎች የህወሀት ታጋዮች የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ዘመናዊ የንግድ ድርጅቶችን ገንብተው እንደሚያከራዩ ይታወቃል።