ለመለስ ፋውንዴሽን ህዝብ የሰጠው መለስ ቀዝቃዛ ነው ተባለ

ጥቅምት ፲፰(አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም መጨረሻ በይፋ የተመሠረተው የመለስ ፋውንዴሽን ዓላማውን ለማሳካት ከሕዝብ ገንዘብ በመዋጮ መልክ ለማሰባሰብ እያደረገ ያለው ጥረት የታሰበውን ያህል ውጤት እያስገኘ አለመሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡

በመለስ ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 781/2005 መንግስታዊ ተቋም ሆኖ የተመሰረተው ይህው ፋውንዴሽን ቤተመጻህፍትና ሙዚየም ለማቋቋም በማሰብ ሕዝቡ ገንዘብ እንዲያዋጣ በየቀኑ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ቅስቀሳ ከተጀመረ ከአምስት ወራት በላይ ቢቆጠርም እየተዋጣ ያለው ገንዘብ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት ፋውንዴሽኑን በበላይነት የሚመሩት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር የአቶ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ራሳቸው አቶ መለስ በሙስናና በውጪ አገር ከፍተኛ ገንዘብ በማከማቸት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና በውጪ አገር በሚገኙና በኢትዮጽያ ላይ ትኩረት ሰጥተው በሚሰሩ ሚዲያዎች ስማቸው በተደጋጋሚ መነሳቱ፣ አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛና የግሉ ዘርፉ ለህዳሴ ግድብ እያዋጣ በመሆኑና በድጋሚ ለማዋጣት ባለመቻሉና በመሰላቸቱ ሊሆን እንደሚችል ተገምቶአል፡፡

ምንጫችን ጨምሮም መዋጮው በውዴታ በባንክ ገቢ የሚሆንና ለጋሹ ስሙን ከማስመዝገብ በላይ መስጠት፣
አለመስጠቱ የማይታይበት በመሆኑ ከፍተኛ የግንባሩ ካድሬዎችና ራሳቸውን የኢህአዴግ ደጋፊ ባለሃብቶች ነን የሚሉት ሳይቀሩ ለመዋጮው እጃቸውን አለመዘርጋታቸው መረጃው ያሳያል ብሎአል፡፡

በአዋጁ መሰረት ፋውንዴሽኑ የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን የሚያርፍበት መናፈሻ መገንባትና ማስተዳደር፣ አቶ መለስ የጻፉዋቸውን ጽሑፎች፣ እሳቸውን የሚመለከቱ ፊልሞች፣የምስል ፣የድምጽና የመሳሰሉት መረጃዎች ተደራጅተው
የሚቀመጡበት ፣ለምርምር በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉበት ቤተመጻሕፍት እንዲያቋቁም ስልጣን ተሰጥቶታል።