ጥቅምት ፲፫(አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 13ኛውን የአርብቶ አደሮች ቀን ለማክበር ደቡብ ኦሞ ዞንን ለማክበር በተገኙበት ወቅት ለእርሳቸው ክብር መገለጫ እንዲሆን እስከ 20 ሚሊዮን ብር እንደፈጀ የሚነገርለት ስታዲያም በጅንካ ከተማ ተስርቶላቸው ነበር።
ይሁን እንጅ ስታዲየሙ ሶስተኛ አመቱን ሳይደፍን ለሁለተኛ ጊዜ ፈርሷል። በመጀመሪያ ከክቡር ትሪቡኑ በስተቀኝ በኩል ያለው ክፍል ፈርሶ ጥገና ሲደረግለት፣ አሁን ደግሞ ክቡር ትሪቡኑ ጥቅምት 10 ቀን ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።
ስታዲየሙ አቶ መለስ ሊመጡ ነው በሚል በ20 ቀናት ውስጥ በይርጋለም ኮንስትራክሽን መገንባቱ ታውቛል።
በሌላ ዜና ደግሞ በጅንካ ከተማ የሚኖሩ በተለይ የኮንሶች ተወላጆች ቤቶች እንዲፈርስ መደረጉን የዞኑ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ስለሺ ጌታቸው ገልጸዋል።
የከተማው አስተዳደር አናፈርስም ብለው ቃል ቢገቡም እንደገና ወደ ማፍረሱ እንደገቡ አቶ ስለሺ ተናግረዋል።
ጀንካ ውስጥ ኮንሶ እየተባለ የሚጠራ ሰፍር ሲኖር፣ ብዙዎቹ የኢህአዴግን የፖለቲካ አቋም ስለማይደግፉና የግንባሩ አባል ለመሆን ብዙዎች ፈቀደና ባለመሆናቸው ብቀላ እንደተወሰደባቸው አቶ ስለሺ ተናግረዋል በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።