ጥቅምት ፲(አስር)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ-ነፃነት እንደዘገበው፦አብረሃ ጅራ እና አብደራጊ የተባሉ ሁለት ወረዳዎች ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ስር የነበሩ ቢሆንም፤ መሬቱ ግን ባብዛኛው በቅርብ ጊዜ ከትግራይ ክልል በመጡ ገበሬዎች ተይዟል፡፡
ቦታዎቹ በብዛትና በስፋት የሰፈሩት ገበሬዎቹች አስተዳደራዊ የበላይነትን በመጠቀም ወረዳዎቹን ወደ ትግራይ ለማካለል እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ጥቅምት 5 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ስብሰባ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመሩ ሲሆን፤ለጉዳዩ ማስፈፀሚያ በማለት ከ500 ሺህ ብር በላይም ማዋጣታቸው ተጠቁሟል፡፡
የጀመሩትን እንቅስቃሴ የአማራ ክልል ባይፈቅድላቸው እንኳ በፌዴራል ደረጃ ማስጨረስ እንደሚችሉ በስብሰባው ላይ ተገልጾላቸዋል።
የሳንጃ፣ የጠገዴ፣ የዳባትና የአፎኛ ደምቢ ወረዳ ነዋሪዎች የገበሬዎቹን ጥያቄ እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።
ድርጊቱን የተቃወሙት የየወረዳዎቹ ነዋሪዎች ጥቅምት 12 በሚጠሩት ስብሰባ- የንግድ ተቋማትን እንደሚዘጉ፣ ስራ እንደሚያቆሙና ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማያደርጉ ማስታወቃቸውን የፍኖተ-ነፃነት ዘገባ ያመለክታል፡፡