ከሊቢያ ወደ ጣሊያን 500 አፍሪካውያ ስደተኞችን ይዛ ትጓዝ የነበረች ጀልባ በደረሰባት የእሳት አደጋ በትንሹ 130 ስደተኞች በአሰቃቂ ሁኔታ መሞታቸው ተሰማ፡፡
ከአቅሟ በላይ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ጣሊያን የሚሄዱ ስደተኞችን የጫነችው ጀልባ በመጨናነቋ ከተሳፋሪዎች አንዱ እርዳታን ለማግኘት ሲል በለኮሰው እሳት ጀልባዋ መቀጣጠሏን አሶሼትድ ፕሬስ ከጣሊያን ዘግቧል፡፡
የእሳት ምልክትን ከሩቅ አይተው ሰዎች ለእርዳታ ይደርሱልናል በሚል የተለኮሰው እሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጀልባዋን በእሳት እንድትጋይ አድርጓታል፡፡
ወደ 500 የሚጠጉትም ተሳፋሪዎች ወደ አለሟት ጣሊያን ሳይደርሱ በሜድትራኒያን ውቅያኖስ ያልታሰበውን አደጋ ለመቀበል ተገደዋል፡፡
እስከ አሁን ድረስ 130ዎቹ የሞቱ ሲሆን ከ150 በላይ የሚሆኑት የገቡበት አልታወቀም፡፡
መዋኘት የማይችሉት ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ውቅያኖሱ እየዘለሉ ቢገቡም ህይወታቸው ማትረፍ ሳይችሉ መቅረታቸውን የጣሊያን ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
አምቡላንስን ሳይሆን የአስክሬን መጠቅለያዎችን ነው የምንፈልገው በጣም አሳዛኝ አደጋ ነው የተከሰተው በማለት ስደተኞቹ ሲያቀኑበት የነበረው የላምፔዱስ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ጊዩስ ኒኮሊኒ ተናግረዋል፡፡
ወደ ከተማ ለመድረስ ሶስት ኪሎ ሜትር አካባቢ ብቻ ቀርቷቸው ከነበሩት 500 ስደተኞች መካከል 159 ብቻ መታደግ ተችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የሟቶቹ ቁጥር ያሻቅባል ተብሎ ተፈርቷል፡፡
ጀልባዋ የኤርትራ፣ ጋና እና ሶማሊያ ዜግነት ያላቸውን ስደተኞች አሳፍራ እንደነበር ታውቋል፡፡
ስደተኞቹን በህገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ሰዎች አደጋ ሲያጋጥማቸው የሳተላይት ስልክን እንደሚጠቀሙ ቢታወቅም ከመንገደኞች አንዱ ግን ሌሎች ጀልባዎች ለእርዳታ ይደርሱልናል በማለት እሳት ለኩሶ ለምልክትነት ለመጠቀም በመሞከሩ አሰቃቂው አደጋ ሊደርስ መቻሉን የጣሊያን ባለስልጣናት በሀዘን ገልጸዋል፡፡
ተሳፋሪዎች ከነበሩበት 100 ሴቶች ሶስቱን ብቻ ከሞት መታደግ የተቻለ ሲሆን የአውሮፖ ህብረት ባለስልጣናት የህገ ወጥ ስደተኞች ዝውውር ትኩረት እንዲደረግበት በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 500 ስደተኞች በህገ ወጥ ዝውውር ምክንያት ወደ ጣሊያን ሲያቀኑ ሞተዋል፡፡