መስከረም ፳፫(ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲዎቹ ባወጡት መግለጫ የሶስት ወር ሕዝባዊ ንቅናቄችን ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ለማጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የከንቲባው ጽ/ቤት መስከረም 3 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ሠላማዊ ሠልፉን በመስከረም 19 ቀን ማድረግ እንደምንችል የሚገልፅ የዕውቅና ደብባቤ ቢሰጠንም ፣ በእጅ አዙር ሠልፉን በመስቀል አደባባይ እንዳናደርግ ከመከልከሉም በላይ ከሕግ ውጨ በመከላከያ በፀጥታ ተቋማት አካባቢ እንድንሰለፍ ለማስገደድ በመሞከርና ቅስቀሳ እንዳናደርግ ክልክሎናል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ አያይዘውም ፖሊስ ህገ መንግስቱንና ህዝቡን መጠበቅ ሲገባው ለመቀስቀስ፣ ፖስተር ለመለጠፍ፣ በራሪ ወረቀቶችን ለማሰራጨት ፈቃድ ያስፈልጋል ትዕዘዝ አልደረሰንም በሚል ተልካሻ ምክንያት ህገ-መንግስታዊ መብታችንን በመጣስ የአንድነትን ሊቀመንበር ጨምሮ በአጠቃላይ 101 አባላትን ከማክሰኞ እስከ እሁድ አስሮብናል ብለዋል፡፡
ፖሊስ ለህግ የበላይነት መቆም ሲገባው በድብቅ ለተሰጠው ትዕዛዝ ተገዥ በመሆኑ ለደረሰው ህገ-ወጥ እስር ፣ ካላግባብ ስለደረሰው የንብረትና የገንዘብ ጉዳት እንዲሁም የሞራል ካሳ የአዲስ አበባ ፖሊስንና የአዲስ አበባ መስተዳድርን በሕግ ለመጠየቅ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
አንድነት እና 33 ፓርቲዎች በጋራ ባዘጋጁት የተቃውሞ ሰልፍ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መንግስት እየፈጸመ ያለውን ሰብአዊ መብቶች ጥሰት አውግዘዋል።
ሰልፈኞቹ በአገሪቱ ውስጥ እየታየ ላለው የኢኮኖሚ ችግር መንግስት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥም ጠይቋል።