መስከረም ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር የሪፐብሊካን እና የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በአዲሱ በጀት ላይ ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ሳቢያ በርካታ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት በከፊል እየተዘጉ ነው።
ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባላት በጀቱን ለማጽደቅ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የህክምና ፖሊሲ ማሻሻያ፤ በእግሊዝኛው አጠራር “ሄልዝ ኬር ሪፎርም” ሊዘገይ ይገባል የሚል አቋምን እንደ ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጠዋል።
በዚህም ምክንያት በፌዴራል መስሪያ ቤቶችና በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ እየሠሩ ያሉ ከ700 ሺ ያላነሱ ሰራተኖች ያለ ምንም የአገልግሎት ክፍያ ከሥራ የመሰናበት ዕጣ እንደተጋረጠባቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
ሁኔታው አሜሪካውያንን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ጭምር ያስደነገጠ ሆኗል።
እንደ ዜና አውታሩ ዘገባ፤ በአሜሪካ በመስሪያ ቤቶችና በልዩ ልዩ ተቋማት ላይ የዚህ ዓይነት የመዘጋት አደጋ ሲያጋጥም- የዶላር ዋጋ እያሽቆለቆለ ከመጣበት ከዛሬ 17 ዓመት ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው።