በአማራ ክልል አንድ የፖሊስ አመራር ተገደለ

መስከረም ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ጎንደር ዞን ደልጊ አካባቢ  ከግጦሽ ሳር ጋር በተገናኘ በተነሳ ግጭት የአካባቢው ኗሪዎች በወሰዱት የመከላከል እርምጃ የፖሊስ አዛዡ ህይወት አልፏል፡፡ የፖሊስ አዛዡ  ነዋሪዎችን ”  መሬት የመንግስት በመሆኑ በተከለከለ ቦታ ላይ ከብቶችን ማሰማራት እንደማይችሉ መናገሩን ተከትሎ ነዋሪዎቹ ” መሬት የኛ መሆኑን ነው የምናውቀው፣ መሬት የህዝብ እንጅ የመንግስት አለመሆኑን ነው የምናውቀው” የሚል መልስ በመስጠታቸው ጉዳዩ ወደ ግጭት አምርቶ ፣ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ ዘጠኝ ኗሪዎች በዱላ በወሰዱት እርምጃ የፖሊስ አመራሩን ገድለው ፤መሳሪያውን ነጥቀው ተሰውረዋል፡፡

ፖሊስ ላለፉት ሶስት ቀናት ገዳዩችን ለመያዝ ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን አልተሰካለትም፡፡ ፖሊስ ገዳዮችን ለመያዝ ባይችልም  የገዳይ ቤተሰብ አባሎች ናቸው የተባሉ ሶስት  የአገር ሺማግሌዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በአማራ ክልል በ2005 ዓ.ም ብቻ 461 የፖሊስ አመራሮች ከህዝብ ጋር በተፈጠረ ውዝግብ ህይዎታቸው አልፎዋል፡፡ ደቡብ  እና ሰሜን ጎንደር ለመንግስት እና ለጸጥታ ሃይሎች ምቹ አለመሆናቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሺን መረጃ ያመለክታል፡፡