መስከረም ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመተከል ዞን በሚገኙ ከተሞች እንዲሁም በአዊ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ካለፉት 3 ወራት ጀምሮ መብራት እንደተቋረጠባቸው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።
በፓዊ የኤሊክትሪክ ሐይል መቆጣጠሪያ እና ማከፋፋያ ዲስትሪክት ስር የሚገኙት እና የቢኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ወረዳዎች፤ወንበራ ፤ ጉባ ፤ድባጢ ፤ ግልገል በለስ ፤ፓዊ ፤ ዳንጉር ፤ ማንኩሺ ፤ማንዱራ ፤ ማንቡክ፤ ቡለን፤ ሞራ ከ500 ሺ ባለይ ህዝብ የሚኖርባቸው ወረዳዎች ሲሆኑ፣ ማንኛውንም የፎቶ ኮፒ ወይም የወፍጮ አገልግሎት ለማግኝት እስከ አሶሳ ከተማ ለመሄድ መገደዳቸው ታውቋል።
በአዊ ዞን ቻግኒ ፤ ጃዊ ፤ ዚገም እና መንታ ውሃ ከተሞች እና ወረዳዎች መብራት በመጥፋቱ እናቶች እህል በእጃቸው እየፈጩ ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ተገደዋል። የኢትዩጵያ ኤሌክትሪክ ሐይል ኮርፖሬሺን ችግሩን ለመፍታት እየሞከርኩ ነው ቢልም እስካሁን አልተሳካለትም።