መስከረም ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዶ/ር ነጋሶ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ሽሮ ሜዳ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ እንዲታሰሩ መደረጉን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ከገለጹ ከሰአታት በሁዋላ ፣ ሊቀመንበሩ ማምሻውን ተፈትተዋል።
አንድ ግለሰብ “የፓርቲው የሰላማዊ ሰልፍ የቅስቀሳ ግብረሀይል አባላት ያለፍላጎቴ ፎቶግራፍ አንስተውኛል” በሚል ክስ መመስረቱን ተከትሎ ፣ የቅስቀሳ አባላቱ መያዛቸውንና እነሱን ለማስፈታት ወደ ስፍራው ያቀኑት ዶ/ር ነጋሶ እንዲታሰሩ ተደርጎ የተያዙት እስረኞች እንዲለቀቁ” መደረጉን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
አንድነት በመጪው እሁድ ለሚያደርገው የተቃውሞ ሰልፍ ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ነው። ፓርቲው ሰልፉን በመስቀል አደባባይ እንዳያደርግ በአዲስ አበባ መስተዳድር መከልከሉን ተከትሎ በአማራጭነት ሌሎች አደባባዮችን ማቅረቡንም አቶ ዳንኤል አክለዋል
ተቃዋሚዎች ሕገመንግስታዊ መብታቸውን መሰረት በማድረግ ከምርጫ 97 በሁዋላ ባልታየ መልኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጠሩት ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ ኢህአዴግን ስጋት ላይ ጥሎታል። ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ከተሞች የሚደረጉ ሰልፎችን በተመለከተ አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል።