መስከረም ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቅዳሜ ከቀኑ 14 ሰዓት ጀምሮ ሙሉ ሌሊቱን ጭምር በደማቅ ሁኔታ በተከበረው የኢሳት 3ኛ ዓመት በዓል ላይ ‘ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።
በዝግጅቱ ኢሳት ከየት ተነስቶ የት ላይ እንደደረሰ በስፋት ያብራሩት የድርጅቱ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነዓምን ዘለቀ፤ኢሳት ለወደፊቱ መድረስ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ የተሰነቀውን ራዕይ ጠቁመዋል።
ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢህአፓው አመራር ዶክተር ዘነበ ተሾመ፤ “ኢትዮጵያ አባትና እናቶቼ የሰጡኝ ሳትሆን እኔ ከ እናትና አባቴ ነጥቄ የወሰድኳት ናት። ስለዚህ የ አሁኑም ትውልድ ከኛ ስጦታ መጠበቅ የለበትም። ነጥቆ መውሰድ ነው ያለበት”ብለዋል።
ያለው አገዛዝ በስልጣን ሊቆይ የቻለባቸውን ምክንያት ሲያስረዱ ኢህአዴግ በተለያዩ ዘርፎች የገነባቸው ሞኖፖሊዎች ዋነኞች መሆናቸውን የተናገሩት የግንቦት 7ቱ አመራር ዶክተር ታደሰ ብሩ በበኩላቸው፤-“ ይሁንና ኢህአዴግ በሚዲያው በኩል ያለው ሞናፖሊ በ ኢሳት ተሰብሯል። ይህም ተጠንክሮ ከተሠራ የማይቻል ነገር እንደሌለ አመላካች ነው፤ በመሆኑም በመከላከያም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ያሉት ሞኖፖሊዎችን ለመስበር ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል”ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ከውጪ መንግስታት ያለውን ግንኙነት ዘርዘር አድርገው ያመለከቱት የ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ የሱፍ ያሲን በበኩላቸው፤ ሆኖም ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማምጣት ለሚደረገው ትግል ገዥው የታጋዮቹ እና የታቃዋሚዎቹ የውስጥ ጥንካሬ እንጂ የውጩ ግንኙነት መድከምና መጠንከር እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በአቶ ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ)ተወካይ ዶክተር አህመድ ሽኩር በበኩላቸው፦ኢትዮጵያውያን በአንድ ተባብረንና ተጋግዘን ለ አንድ አገር ግንባታ ወደፊት እንድንራመድ ባለፉት ሥርዓት በተለያዩ ብሄረሰቦች ላይ በተፈፀሙ የታሪክ በደሎች ላይ በማያሻማ መልኩ መስማማትና ዳግም እንዳይፈፀሙ መተማመን አለብን ብለዋል።
“አጼ ምኒልክ በአድዋ በፈፀሙት ገድልና የአፍሪካ የነፃነት መሪ በመሆናቸው እኔም እኮራባቸዋለሁ” ያሉት የኦነጉ ተወካይ፤ “ያ ማለት ግን በአስተዳደራቸው ጊዜ በአገር ውስጥ የተፈጸሙ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም።በሁሉም ባይሆን ከፍ ከፍ ባሉት የታሪክ በደሎች ላይ መስማማታችን ወደፊት ለምናደርገው ጉዞ መተማመን ይፈጥራል”ብለዋል።
አክቲቪስት ወይዘሮ አሳየሽ ታምሩ በበኩላቸው አምባገነናዊውን አገዛዝን ለማስወገድ ወሳኙ ትግል መደረግ ያለበት በአገር ቤት ውስጥ መሆኑን በማመን ዲሞክራሲያዊና ነፃነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት የምንሻ በውጪ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በ አገር ውስጥ የሚደረገውን ትግል እንደ አቅምና ችሎታችን ልንደግፍ ይገባል ብለዋል።
የቀድሞው የህወሀት ታጋይ አቶ ገብረመድህን አርአያ በስካይፒ ባደረጉት ገለፃ፤ የህወሀት አስተዳደር በመጨረሻው ቋፍ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ጠቅሰው ካብራሩ በሁዋላ፤ ሥርዓቱን በሀይል መደምሰስ የመጀመሪያውና ቀዳሚው አማራጪ ነው ብለዋል።
በምሽቱ ፕሮግራም ላይ ተጋባዥ የነበረችው አርቲስት በዛወርቅ አስፋው እና አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ታዳሚዎችን አዝናንተዋል።
የኢሳት 3ተኛ ዓመትን አስመልክቶ የነበረውን ሙሉ ዝግጅት ከሰሞኑ ይዘን እንቀርባለን