መስከረም ፮(ስድት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አዲስ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) አፈጻጸም እጅግ አነስተኛ እንደነበር ከኢንዱስትሪ ሚ/ር የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡
በ2005 የኢትዮጵያዊያን በጀት ዓመት ከጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ከአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ከፋርማሲዩቲካልስና ከኬሚካል የወጪ ንግድ 542 ሚሊዮን 4 መቶ ሺ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 281 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ዶላር ወይንም 52 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው፡፡ ዘርፉን ባለፉት ሁለት ዓመታት በ18 በመቶ ለማሳደግ በመንግስት በኩል እቅድና ፍላጎቱ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን እቅድ ማሳካት የተቻለው በ12 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ለዚህ ከተሰጡ ምክንያቶች መካከል የአቅም ውሱንነት፣የምርት ጥራትና ምርታማነት ማነስ፣ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር አለመቻልና የተገኙትንም አሟጦ መጠቀም አለመቻል እንዲሁም የሰው ኃይል እጥረት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ከ2003-2007 ዓም መንግስት ባወጣው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ቀደም ሲል ኢኮኖሚው ግብርና መር ነው በሚል ሙጭጭ ያለበትን አቋሙን በማስተካከል እስከ 2007 ዓ/ም ድረስ ኢንዱስትሪው መሪነቱን ከግብርና የሚረከብበት ሁኔታ እንደሚኖር በእቅዱ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የአጠቃላይ ኢኮኖሚው ደካማ አፈጻጸም ኢንዱስትሪን እና ግብርናን በማዳከም በአንጻሩ ከእቅድ ውጪ የአገልግሎትን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ደካማ አፈጻጸም አንድ ዓመት ገደማ የቀረውን የመንግሰት የትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደማይሳካ ከወዲሁ ጠቋሚ ሆኗል፡፡