ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የቤተመንግስት ኑሮ የሚመች አለመሆኑንና የቀድሞ ጠ/ሚኒስትርንም አኗኗር በማየት ያዝኑ እንደነበር ተናግረዋል።
ቀዳማዊት እመቤቷ ትላንት ከወጣው መንግስታዊው ዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የቤተመንግስት ሕይወት አስደሳች አይደለም ብለዋል፡፡ “ የቤተመንግስትን ሕይወት ለማንም ተመኝቼው አላውቅም፡፡ የሴቶች ጉዳይን ስናቋቁም ስምንት ወር ተመላልሼበታለሁ፡፡ ዛሬ እናንተ ተፈትሻችሁ እንደገባችሁት እኛም ተፈትሸን ነበር የምንገባው፡፡ እዚህ ግቢ ስገባ ወደጠ/ሚኒስትሩ ቤተሰቦች መኖሪያ ማዶ እያየሁ አዝንላቸው ነበር፤ግን ለሰው አላወራም፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ የሚኖር ሰው እንዴት ተበድሎአል እያልኩ እገረም ነበር፡፡ እና እኔን ኑሪ ቢሉኝ የማላደርገው መስሎ ይሰማኝ ነበር፡፡ ብለዋል፡፡
አስተዳደጌ ያስተማረኝ ከሌሎች ጋር በጋራ መኖርን ነው ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ራስን ለማዝናናት፣ዞር ብሎ ቡና ለመጠጣት ፣ዘመድ ጓደኛ እንደልብ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ አንጻር የቤተመንግስት ሕይወት ነጻነት የለውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“ለአንዳንዶች የቤተመንግስት ሕይወት የተንደላቀቀ መስሎ ይሰማቸዋል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም በአጭሩ እንደሚታሰበው ዓይነት አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የቀድሞ ኑሮአቸው ከአሁኑ በምን ይለይ እንደሆነ ተጠይቀውም የምግብ ማብሰያውና የአዘገጃጀቱ ሁኔታ ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ “ቤተመንግስት የበሰለው ነገር በንጽሕና የሚቀርብበት ነው፡፡ አዘጋጆቹ በዘርፉ ሙያው ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙ ዓመት ያገለገሉ ወጥ ቤቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ እንግዲህ ጥበቃው አለ፤ይህው ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡
ወ/ሮ ሮማን ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አብራክ የወለዱዋቸው የ23፣የ20 እና የ18 ዓመት ሶስት ሴት ልጆች እንዳሉዋቸውም በቃለምልልሳቸው ተናግረዋል፡፡
ባለቤታቸው አቶ ኃይለማርያም በአመራራቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማቸው እንደሆን ተጠይቀውም ሲመልሱ አስቸጋሪ ነገር እንኩዋንስ አገር የሚያክል ነገር በመምራት ላይ ቀርቶ ታችም ሞልቱዋል፡፡ “አሁን ያለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው፡፡ ብዙ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያላቸው ጠቃሚም ጎጂም ነገሮች አሉ፡፡ የኢትዮጽያ ሕዝብ አሁን ለመብቱ መታገል ተለማምዶአል፤ መጠየቅን ለምዶአል፡፡ ፈጣን ዕድገትን ይፈልጋል፡፡ ሠላምን፣ ተረጋግቶ መኖርን ይፈልጋል፡፡ መልካም አስተዳደርን ይፈልጋል፤ መልካም አስተዳዳር ሲባል ደግሞ በውስጡ ብዙ ጉዳዮች አሉት፡፡ እና ይህን ሁሉ ፍላጎት ይዞ ሕዝብን የሚያረካ አመራር መስጠት እያደገ የሚሄድ ነው” ብለዋል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ከቀድሞዋ እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን ተረክበው ከባለቤታቸውና ልጆቻቸው ጋር የቤተመንግስት ኑሮ ከጀመሩ ገና አንድ ዓመት አልደፈኑም፡፡
ወ/ሮ ሮማን የቤተ-መንግስት ኑሮ ነጻነት እንዳይኖረው የተደረገበትን ምክንያት አላብራሩም፣ ነጻነት እንዲኖረው ለማድረግም ምን ምን እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አልዘረዘሩም። ወ/ሮ ሮማን ህዝቡ ስለመብቱ መታገል ተለማምዷል በማለት መናገራቸው በቅርቡ የተቃዋሚ ድርጅቶች ካደረጉት ሰልፍ ጋር ይያያዝ አይያያዝ ወይም፣ ይህ ልምምድ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ ፣ በአቶ ሀይለማርያም የስልጣን ጊዜ የመጣ ክስተት መሆኑንና አለመሆኑን አላብራሩም።