ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ታዋቂው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ቢሮክራሲ የኢንቨስትምንት ስራ ለመስራት ዋነኛው እንቅፋት መሆኑን ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጿል። የመብራትና ውሀና መንገድ ችግሮችን በጋራ መቋቋም ይቻላል ያለው ሀይሌ ፣ ቢሮክራሲው ከፍተኛ ችግር መሆኑን ገለጿል።
ሀይሌ እንደሚለው የቢሮክራሲው ዋና ምክንያት በራሳቸው የሚወስኑ ባለስልጣናት መጥፋታቸው ነው። በተለያዩ ሀላፊነት ላይ ያሉ ባለስልጣናት በራሳቸው እንዲወስኑ እስካልተደረገ ድረስ ችግሩ ሊፈታ እንደማይችልም ተናግሯል።
በኬንያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ድርጅቶች በመኖራቸው ህዝቡ አማርጦ እንደሚገዛ የገለጸው ሀይሌ፣ በኢትዮጵያ እንዲህ አይነት እድል ባለመኖሩ መስሪያ ቤቱ ውጤታማ አለመሆኑን አብራርቷል። መብራት ሀይልም እንዲሁ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ ሊገባ እንደሚገባው አትሌቱ መክሯል።
አትሌት ሀይሌ በቅርቡ ወርቅ በማውጣት ስራ ላይ ለመሰማራት ማቀዱንም ገልጿል። የኢትዮጵያ አትሌቶች በከፍተኛ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ መሰማራታቸውን አክሎ ተናግሯል።
ታዋቂው አትሌት ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት እንዳለው መግለጹ ይታወሳል።