ኢትዮጵያውያን ነገ በዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ ይወጣሉ

ሃሴ ፳፫(ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እየተካሄደ ያለውን የሙስሊም ማህበረሰብ ጥያቄ የማፈን ተግባርን በመቃወም ነገ በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ የሰልፉ አስተባባሪ አካላት ለኢሳት ገለጹ፡፡

የአርብ የፀሎትና የስግደት ስነ ስርዓትን ተከትሎ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በሀገር ቤት እየተካሄደ ያለውን የመንግስት እርምጃ ለማውገዝ ያለመ እንደሆነ የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሰይድ አብዱራህማን ተናግረዋል፡፡

የሙስሊሙን ጥያቄ ለማፈን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከመቼውም ጊዜ በባሰ መልኩ ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየሄደ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሰይድ የሙስሊሙም ሆነ የሌላው ሀይማኖት ተከታይ አክራሪነትን የመዋጋት ሀላፊነት እንዳለባቸው ጠንቅቀው እንደሚያውቁ አስታውቀዋል፡፡

አዲስ የተጀመረው የገዥው መንግስት አካሄድ አክራሪነትን ሳይሆን አንድን ሀይማኖት ያነጣጠረ በሚመስል መልክ እየተፈፀመ እንደሆነና ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ስጋትን መፍጠሩን አቶ ሰይድ አስታውቀዋል፡፡

ነገ በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የተለያዩ የሀይማኖት ተከታዮች አንድነታቸውን የሚያሳይ መፈክርን በማሰማት የአሜሪካን መንግስት እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትኩረት እንዲሰጥ እንደሚጠይቁ ይጠበቃል፡፡

የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ መልስ መስጠት የተሳነው ገዥው መንግስት ጥያቄያቸውን ሌላ መልክ ለመስጠት የሚያስችል ሰላማዊ ሰልፍ በመጪው እሁድ መጥራቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡