ነሃሴ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አራቱ የደቡብ ክልል ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ከፍተኛ ሀላፊዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኙ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡
የክልሉ ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊው አቶ ውብሸት ፀጋዬ፣ የግዢና ፋይናንስ ንብረት አስተዳደር ሀላፊው አቶ ይገረሙ ፋሲቆ፣ የክፍያዎች ሀላፊው አቶ አቦሰጥ መብራቱ፣ መሐንዲሱ አቶ ሞገስ ዩሀንስ እና ኮንትራክተር የነበሩት አቶ ተክለወልድ ማሞ በቁጥጥር ስር የሚገኙ ሀላፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
አራቱ ባለስልጣናት በጋራ በመሆን በሲዳማ ዞን በበንሳ ወረዳ በመካሄድ ላይ በነበረ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከፍተኛ የሆነን ገንዘብ ለግል ጥቅም በማዋል በሚል መታሰራቸው ተገልጿል፡፡
ባለፈው ወር አስራ አራት የሚሆኑ የኦሮሚያ ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ከሙስና ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና ከታሰሩ ዘጠና ቀናት የሞላቸው የኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣናት በመጪዎቹ አስራ አምስት ቀናት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ዋና ሀላፊ አቶ መላኩ ፈንታና ስልሳ ሶስት የጉምሩክ ሀላፊዎች በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ምርመራቸው በመጠናቀቁ ክስ ማሰማት ሂደቱ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡
የኢንተር ኮንቲኔታል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ፣ የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም የሆኑት አቶ ምህረተአብ አብርሃ እና የበርካታ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት የሆኑት አቶ ከተማ ከበደ በቁጥጥር ስር ከሚገኙት 63 ሰዎች መካከል ናቸው፡፡