ነሃሴ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስትን ከአካባቢው ማግኘት የነበረበትን ከ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር መሰብሰብ እንዳልቻለ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ጠቆመ፡፡
የመንግስትን የገቢ ግብር መሰበሰብ ያልተቻለው የአዲስ አበባና የአገሪቱ የንግድ ማዕከል በሆነው በመርካቶ አካባቢ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲከናወን የቆየው የግብይት ስርዓት በአብዛኛው ሕገወጥ በመሆኑ ነው ብሏል። ይህንን ችግርም
ለመቅረፍ ባለሰልጣኑ የመርካቶ አካባቢን የታክስ ሕግ ተገዢነት ለማሻሻል ፕሮጀክት ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡በዚሁ ፕሮጀክት ጥናት መሠረት በመርካቶ አካባቢ 75 በመቶ ያህል ነጋዴ በሕገወጥ መልኩ ታክስና ግብር ሳይከፍል
የሚሠራ ነው፡፡
የባለስልጣኑ መረጃ እንደሚያሳየው በመርካቶ አካባቢ ለግብር ከፋዩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልና ፍትሃዊ ግብይት የሰፈነበት ስፍራ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ለንግዱ ማህበረሰብ ስለግብር ትምህርት መስጠት ፣ ለህግ ተግዥነትን ለማሳደግ የሚረዱ እርምጃዎች መውሰድና መረጃዎችን ከሶስተኛ ወገን መሰብሰሰብ እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ጥናት መሰረት በመርካቶ አካባቢ እየተከፈለ ያለው የታክስ መጠን እጅግ አነስተኛና ከ25 በመቶ የማይበልጥ መሆኑን እንደሚያመለክት በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ ተጨማሪ ሁለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ስድስት የገቢ መስብሰቢያ ማዕከላት ሁኔታውን ለመቀየር እየሞከሩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ካለፈው አንድ አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ በመርካቶ አካባቢ ልዩ ትኩረት አድርጎና ከፍተኛ በጀት መድቦ መንቀሳቀስ የጀመረው ሕዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ካነሳ በኃላ መሆኑን የመረጃው ባለቤቶች ጠቅሰዋል።