ነሃሴ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢድ አልፈጥርን በዓል ለማክበር ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አስራ ሁለት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለኢሳት አስታወቁ፡፡
አራት የአሜሪካ፣ ሁለት የሲዊዲን፣ አንድ የአውስትራሊያና አምስት የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያኑ ከትላንትናው እለት ጀምሮ በማዕከላዊ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ውለው በነበረበት ወቅት እየተካሄደው ያለው የሙስሊዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከውጭ ሀይሎች ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ ለማስመሰል በመርማሪዎች የተሳሳተ መረጃ እንዲሰጡ ጫና እየተደረገባቸው እንደነበር ቤተሰቦቻቸው ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
በኢዲስ አበባ በኢድ አልፈጥር በዓል ወቅት ቁጥራቸው 2ሺህ የሚጠጋ የሙስሊም ተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተለያዩ አካላት የገለጹ ሲሆኑ ፌደራል ፖሊስ ምን ያህል ሰው በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ከመግለጽ ተቆጥቦ የተያዙት ሰዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀይለ ማርያም ደሳለኝ እየተካሄደ ያለው የሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ‹የሸርያን መንግስት ለመመስረት› ያለመ እንቅስቃሴ በማለት የውጭ ሀይሎች እጅ እንዳለበት በመናገር ለማስተባበል መሞከራቸውን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ‹ከእኛ ጥያቄ ውጭ› የሆነ ንግግር ነው በማለት በመቃወም ላይ ይገኛሉ፡፡