ከ 27 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለ የቴሌኮሙኒኬሽን ማስፋፊያ ሥራ ለቻይና ኩባንያ ተሰጠ።

ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከስልክ ኔትወርክ ጥራት ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚነሳውን ቅሬታ ይፈታል የተባለ እና 1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ 27 ቢሊዮን ብር በላይ  ወጪ የጠየቀ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ ”ሁዋዌ”ለተሰኘው  የቻይና ኩባንያ ትናንት ተሰጠ።

የፕሮጀክቱን ውል ስምምነት ትናንት ማምሻውን ኢትዮ ቴሌኮም  እና የቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ ጋር ተፈራርመዋል።

ፊርማውን የኢትዮ ቴሌኮም ተቀዳሚ ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም አድማሴ ፤ በሁዋዌ በኩል ደግሞ የኩባንያው ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ጆኒዱኦን ያስቀመጡ ሲሆን ፥ በአጠቃላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ላይም ከሁዋዌ በተጨማሪ የዜድ ቲ ኢ የቴሌኮም ኩባንያም የቴሌን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ተሳታፊ ይሆናል ተብሏል።

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ  በዋናነት ለጥራት ትኩረት በመስጠቱ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሲጠናቀቅ አሁን የሚስተዋለውን የኔት ወርክ ጥራት ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበትም   ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል  ተናግረዋል።

የሁዋዌ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጆንዱንግ በበኩላቸው ፥ ፕሮጀክቱን በፍጥነት በማጠናቀቅ የተሻለ የቴሌኮም አገልግሎት በቅርቡ ለማሰረከብ ቃል ገብተዋል።

ይሁንና የቻይናው ህዋዌ ኩባንያ ይህን ያህል ትልቅ ፕሮጀክት-ከ ኢትዮ ቴሌኮም የተረከበው በግልጽ ጨረታ ይሁን አለያም እንደተለመደው እንዲሁ ተሰጥቶት፤አቶ ደብረጽዮን ያሉት ነገር የለም።

ቻይና ለ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እየሰጠች ያለች አገር ነች።

ሁዋዌ የተባለው የቻይና ኩባንያ የአሜሪካን መንግስት ይሰልላል በሚል ክስ ቀርቦበት እንደነበር ይታወቃል። ኩባንያው ለኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ሶፍትዌሮችን ሊሰጥ መስማማቱን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።