ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ከተማ በሆነችው በሳንቲያጎ ደ-ኮምፖስቴላ ረቡዕ እለት በደረሰው የባቡር አደጋ 78 ሰዎች ሲሞቱ 130 ሰዎች ተጎድተዋል።
ከ130ዎቹ ቁስለኞች መካከል 35 ቀላል እርዳታ ተደርጎላቸው ከሆስፒታል የወጡ ሲሆን ከበድ ያለ ጉዳት የደረሰባቸው 95 ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ።
የባቡሩን ሾፌር ለአደጋው ተጠያቂ ያደረገው የስፔን ፖሊስ ፤አደጋው በሚደርስበት ጊዜ ባቡሩ ከተፈቀደው ፍጥነት ከእጥፍ በላይ እየከነፈ እንደነበር ጠቁሟል።
የመቁሰል አደጋ የደረሰበትና ላደጋው ተጠያቂ የሆነው ሾፌር በአሁኑ ጊዜ በ አጃቢዎች እየተጠበቀ ህክምናውን እየተከታተለ ነው።
ከተጎዱት መካከል 32ቱ ክፉኛ መቁሰላቸውን ያመለከተው ቢቢሲ፤ ከነዚህም ውስጥ ከተለያዩ የ ዓለማችን ክፍሎች የመጡ ዜጎችና ህፃናት ጭምር እንደሚገኙበት ዘግቧል።
አደጋውን ተከትሎ በስፔን መጪዎቹ ሦስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ጊዜ እንዲሆኑ ታውጇል።