የዱከም ድልድይ ግንባታ ውል እንዲቋረጥ ተወሰነ

ሐምሌ ፲፰(አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ዕቃዎች የሚስተናገዱበት ዋና ጎዳና ላይ የዱከም ድልድይን ለመገንባት የተረከበው አክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሥራውን በውሉ መሠረት ባለማከናወኑ የኮንትራት ውሉ እንዲቋረጥ መወሰኑ ተገለጸ፡፡

ሪፖርተር ምንጮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው  “ጎጊቻ” በሚባለው ወንዝ ላይ የተጀመረው የድልድይ ግንባታ በውሉ መሠረት እየተከናወነ ባለመሆኑና የግንባታው መጓተት እያስከተለ ያለውን ችግር ከግምት በማስገባት፣ ከኮንትራክተሩ ጋር የተገባው ውል እንዲቋረጥና ሥራው ለሌላ ተቋራጭ እንዲሰጥ ተወሰኗል፡፡ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈውም- የድልድዩን ግንባታ በባለቤትነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ባለስልጣኑ- የድልድይ ግንባታው መዘግየቱን ተከትሎ አሁን የደረሰበትን ውሳኔ ለኮንትራክተሩ ያሳውቃል ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ኮንትራክተሩ ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ በተደጋጋሚ ደብዳቤ የተጻፈለትና ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ቢሆንም፣ ሥራውን ለማጠናቀቅ አለመቻሉን የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሮት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለጋዜጣው ገልጸዋል፡፡
የአገሪቱ የገቢና የወጪ ዕቃዎች የሚስተናገዱበትን የዚህን ድልድይ ሥራ ማዘግየት ተገቢ አይደለም ሲሉም አቶ ሳምሶን ጨምረው ገልጸዋል።

ለዚህ ድልድይ ግንባታ ተብሎ ቀደም ብሎ የነበረው ድልድይ ፈርሶ በብረት ተለዋጭ ድልድይ ተሠርቶለት ተሽከርካሪዎች እየተስተናገዱበት  ቢሆንም፤ ተለዋጩ ድልድይ ከፍተኛ መጠን ያለው ጭነት እያስተናገደ በመሆኑ ጥገና በሚደረግበት ወቅት በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ከዚህም በላይ ተጠቃሚዎችም ድልድዩ ይፈርስብን ይሆናል የሚል ሥጋት እያደረባቸው በጥንቃቄ ተራ በተራ እየተጠባበቁ የሚሻገሩ  ሲሆን፤አንዳንዴ በጊዜያዊ ድልድዩ ላይ ለማለፍ የሚጠባበቁ ተሽከርካሪዎች ተራ ለመጠበቅ ረዥም ሠልፍ ይዘው የሚቆሙበት አጋጣሚም አለ፡፡
የዚህ ድልድይ ግንባታ ሥራ ለአክሽን ኢንጂነሪግ ኩባንያ የተሰጠው በየካቲት 2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ መጠናቀቅ የነበረበት መጋቢት 2005 ዓ.ም. ነበር።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት የተሠራው ሥራ ግን ግማሽ ያህል እንኳን አለመድረሱ ታውቋል፡፡

ድልድዩ 45 ሜትር ስፋት ሲኖረው፣ ኩባንያው በወቅቱ ድልድዩን ለመሥራት ኮንትራክተሩ አሸንፎበት የነበረው ዋጋ 11.16 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ለዚህ ድልድይ ግንባታ ሥራ መጓተት ዋነኛ ምክንያት የአቅምና የፋይናንስ ችግር ነው ያሉት አቶ ሳምሶን፤ ባለሥልጣኑ የግንባታ ሒደቱን በተለያየ ጊዜ ፈትሾ ኮንትራክተሩና አማካሪ መሐንዲሱ ጭምር ተጠርተው አስፈላጊው መመርያ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡
የአገሪቱ ዋነኛ የገቢና ወጪ ማስተናገጃ መንገድ ላይ የሚሠራው ይህ ድልድይ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ከማስተናገዱ አንፃር የግንባታው መጓተት ትልቅ  ማነቆ መሆኑንም ባለሥልጣኑ ያምናል ያሉት አቶ ሳምሶን፣ ሥራው ለሌላ ኮንትራክተር የሚሰጥ ከሆነ በአስቸኳይ እንዲያልቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው: “በአሁኑ ጊዜ ግንባታው እየተካሄደ አይደለም፤አልፎ አልፎ ይታዩ የነበሩ ሠራተኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጭራሽ አይታዩም፡፡ መንግሥት ለውሳኔ ይህን ያህል ጊዜ መዘግየቱም አግባብ አይደለም “ይላሉ፡፡