የፓርላማው ውይይት መታፈኑን ያጋለጠው የኢቲቪ ጋዜጠኛ ከሥራ ተባረረ

ሐምሌ ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናና የአስፈፃሚ ተቋማት ኃላፊነት” በሚል ርዕስ ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ያደረገውን ውይይት በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በኩል ተቆራርጦና ተዛብቶ እንዲተላለፍ ተደርጓል በሚል አንድ ዜና መዘገቡ ይታወሳል።

ዜናው በሰንደቅ ጋዜጣ የህዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም ዕትም “ኢቲቪ የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውይይት በማፈን ተወቀሰ” በሚል ርዕስ ከቀረበ በኋላ፤ በዚህ ዘገባ ላይ ተመድቦ የሠራው የቀድሞ የኢቲቪ ባልደረባ ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ ረቡዕ ህዳር 12 ቀን 2005 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ  ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም።

ዜናዎቹ መዘገባቸውን ተከትሎ ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ ለሚዲያዎች መረጃ እንደሰጠና ሚስጢር እንዳወጣ ተቆጥሮ የዲስፒሊን ክስ ቀርቦበታል።

የኢትዮጵያ .ሬዲዮ እና.ቴሌቪዥን  ድርጅት በዲስፒሊን ክሱ ላይ  አራት ከፍተኛ የሥራ አመራሮችን በምስክርነት ዘርዝሮ አቅርቧል።

የድርጅቱ የዲስፒሊን ኮሚቴ በከሳሽ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና በጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ መካከል የክስ ዝርዝር እና የመልስ መልስ ደብዳቤዎች ሲያዳምጥ ከሰነበተ በኋላ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም በቁጥር ቴ02.1/131-304/02/8/ በተፃፈ ደብዳቤ ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ  ከግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ እንዲሰናበት የሚል ቅጣት አሳልፏል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባለቤትነት በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም የተካሄደው ስብሰባ በመልካም አስተዳደር፣ በተጠያቂነት፣ በሙስና ችግሮችና በመሳሰሉት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህ ውይይት ላይ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና ቀደም ሲል የትምህርት ሚኒስትር ጭምር የነበሩት  አቶ ደመቀ መኮንን ፣የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሐዬ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ የእምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አበባው ስጦታው እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር።

ም/ቤቱ የጠራውንና የአስፈፃሚ አካላትና የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናን በተመለከተ ያደረገውን ውይይት፣ በዕለቱ በሥፍራው ባልነበረ ጋዜጠኛ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ተቆራርጦና ተዛብቶ ለሕዝብ መቅረቡ ትክክል እንዳልነበረ በይፋ በመግለፁ ምክንያት  ነው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ ከሥራ የተሰናበተው ።