መንግስት ሕዝበ ሙስሊሙን ለማውገዝ የሠላም ኮንፈረንስ ጠራ

ሐምሌ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር  የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላትን በማንቀሳቀስ አገር አቀፍ የሠላም ኮንፈረሰንስ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ይፋ አደረገ፡፡

መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ ሕገመንግስቱ ቢደነግግም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሕገመንግስት አስተምህሮ ስም የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጭምር በማቋቋም የመብት ጥያቄ በማቅረባቸው ምክንያት የታሰሩና የሽብርተኝነት ክስ የቀረበባቸውን የሕዝበ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላትና ደጋፊዎቻቸውን እንቅስቃሴ ለማፈን አሁንም
በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሙስሊም ጉዳዮች አስተባባሪ ለኢሳት ዘጋቢ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር “ሀይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር እሴት በማጎልበትና ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የሀገራችን ሕዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረብ” በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ ከነሐሴ 21 – 23 ቀን 2005 ዓ/ም ድረስ የሃይማኖቶች የሰላም ኮንፈረንስ እንደሚያካሂድ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ኮንፈረንስ የዘጠኙ ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል የሚካሄድና    በፌዴራል ደረጃ በሚካሄደው ኮንፈረንስ የሚጠናቀቅ ሲሆን ሰፊ የሕዝብ ንቅናቄ ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጿል።

ይህ አዲስ አካሄድ መንግስት የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ እጅግ ዘግይቶና ብዙ በደሎች ተፈጽመውም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎት እንደሌለው የሚጠቁም ነው በማለት አስተያየት ሰጪው ገልጸዋል፡፡ መንግስት የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች ከመመለስና የመብት ጥያቄ በማቅረባቸው ምክንያት የታሰሩት የመፍትሔ አፈላላጊ ኮምቴ አባላትን ከመፍታት ይልቅ ሙስሊሙን ደጋፊና ተቃዋሚ በሚል ለሁለት ከፍሎ እርስ በእርስ ለማጋጨት እያደረገ ያለው ጥረት አደገኛ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል አስተያየት ሰጪው አክለው ገልጸዋል።
የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ አፍኖና አግልሎ የሚደግፉትን ሰዎች ብቻ በመሰብሰብ የሠላም ኮንፈረንስ ማካሄድና በዚህም የሕዝብና የመንግስትን በጀት ማጥፋት ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት ጨርሶ የማይጠበቅ ተግባር መሆኑንም አስተባባሪው ተናግረዋል።

ይህን የሃይማኖቶች የሰላም ኮንፈረንስ ዓላማና ዝግጅት አስመልክቶ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በጋራ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።