ሐምሌ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኒዮን የስዊዘርላንድ ከተማ የተካሄደው 11ኛው የአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ቅዳሜ ጁላይ 20 በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት፣ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከተለያዩ አህጉራት የመጡ በርካታ ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለበዓሉ ድምቀት አስተዋጽዖ አድርገዋል።
ይህ በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላለፉት 11 ዓመታት በተከታታይ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የሚገኙና ከሌሎች አህጉራትም ጭምር በመሰባሰብ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበትና በድምቀት የሚያከብሩት ፌስቲቫል ነው።
በዚህ ፌስቲቫል ይሳተፋሉ የተባሉት የእግር ኳስ ቡድኖች በአንደኛ ዲቪዚዮን 18 ሲሆኑ፣ በአራት ምድብ ተከፍለዋል። በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ 8 ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው ውድድሩን አካሂደዋል። ከአውሮፓ 24 ቡድኖች፣ ከዩናይትድ ስቴትስ አንድ እና ከደቡብ አፍሪካ አንድ ናቸው።
በዚህ ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋችና አሠልጣኝ የነበሩት አቶ ወርቁ ደርገባ ናቸው።
ቅዳሜ በተደረገው የዋንጫ ውድድር የአዘጋጁ አገር ቡድን ኢትዮ ስዊስ ተጋጣሚውን የእንግሊዝ ቡድን በ ጨዋታ ብልጫ 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን ለሶስተኛ ጊዜ ወስዶ የግሉ አድርጓል::
እንዲሁም አዘጋጁ የኢትዮ ስዊዝ ቡድን ያማረ ውድድር ከማዘጋጀቱና ሻምፒዮን ከመሆኑ በተጨማሪ የውድድሩን ኮከብ ተጨዋች ኮከብ ግብ አግቢና ኮከብ በረኛ በማስመረጥም ባለ ድል ሆኗል፡፡
ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ እና ታዋቂው አርቲስትና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ታማኝ በየነ እንዲሁም የቀድሞው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንና የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ተጫዋች የነበረው ክርስቲያን ካሬምባ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል።
በዝግጀቱ ማጠቃለያ ላይ ታዋቂው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ዝግጅቱን አቅርቧል::
የስፖርቱን ሂደት በተመለከተ የተቀናበሩ ዝግጅቶችን በቅርቡ እንደምናስተላልፍ ለመግለጽ እንወዳለን።