ሐምሌ ፲፭(አስራ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የግንባሩ 9ኛ ጉባዔ ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2003 እና በ2004 ዓ.ም ግንባሩ 88 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን ቀድሞ በባንክ አካውንት ውስጥ ከነበረው ሒሳብ ጋር ሲደመር ገቢው 171 ነጥብ 2 ሚሊየን መድረሱንም ይፋ አድርጓል፡፡
46 በመቶ የሚሆነው ገቢ የተገኘው ከ“አዲስ ራዕይ” እና “ህዳሴ” ከተሰኙ ሕትመቶች ሽያጭ ነው ፡፡ ቀሪው 54 በመቶ የተገኘው ደግሞ ከአዲስአበባና ድሬዳዋ አባሎቹና ከአባል ድርጅቶች ከሚያገኘው ፈሰስ ነው፡፡ ግንባሩ የሚያወጣቸውን በመቶ ሺዎች ቅጂ ሕትመቶች በየቀበሌውና ወረዳው ለአባላቱና ደጋፊዎቹ ከደመወዛቸው ጭምር እየተቆረጠ ገቢ የሚያደርግ በመሆኑ ግንባሩ ከሕትመቶቹ እንደፋብሪካ እንዲያተርፍ አስችሎታል፡፡
አንድ የኢህአዴግ አባል አ/አ ለሚገኘው ዘጋቢያችን እንደተናገረው በርካታ የግንባሩ አባላት የቀድሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ አዲስ ራዕይ፣ ህዳሴ፣ ወይን እና ሌሎችም ልሳናትን የሚገዙት በግዴታ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ አባላት እንደማያነቡዋቸው ጠቁሟል፡፡
በተለይ አዲስ ራዕይ የሚባለው መጽሔት የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች የሚጽፉበት፣ መጽሔቱ ከወጣ በሁዋላም አባላት በየደረጃው እንዲወያዩበት እንደሚደረግ አስታውሶ ይህም ሆኖ ጥቂት የማይባሉ አባላት ምንም ፍላጎት ካለማሳየታቸው ጋር ተያይዞ የሚይዙት ፍሬ ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡
ግንባሩ ለድርጅቱ ሕንጻ መገንቢያ 43 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በልዩ ሁኔታ መሰብሰቡን በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ሆኖም ይህ ገቢ ከእነማን በምን ሁኔታ ተገኘ የሚለውን ያብራራው ነገር የለም፡፡ ሌሎች ምንጮች ግን ይህ ገቢ የኢህአዴግ ደጋፊ ከሚባሉና በአመዛኙ ኢህአዴግን ተጠግተው፣ ከሚነግዱ ጥቂት ባለሃብቶች የተሰበሰበ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከነዚህ ባለሃብቶች መካከል በአሁኑ ወቅት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ጋር በሙስና ክስ የቀረበባቸው የኬኬ ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ፣ የአዲስ ልብ ሆስፒታል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ የነጻ ትሬዲንግና የባሰፋ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር፣ የአልትሜት ፕላን እና የኢትባ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ በእግዚአብሔር አለበል እንደሚገኙበት ምንጫችን ጠቁሟል፡፡