ግንቦት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሪፖርተር እንደዘገበው የመስኖ እርሻና የሶዳ አሽ ሥራዎች ለአብያታ ሐይቅ ህልውና አደጋ መሆናቸውን ምሁራን ናቸው ያስጠነቀቁት በአንድ ወቅት በዝዋይ በሚገኙ የአበባ እርሻዎች ሳቢያ ለብክለትና ለከፍተኛ የውኃ መጠን መቀነስ ችግር ተዳርጎ የቆየው አብያታ ሐይቅ፣ በአሁኑ ወቅት በመስኖ እርሻዎችና ሶዳ አሽ በሚያመርተው ፋብሪካ ሳቢያ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጧል።
ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ከአንድ ትውልድ በላይ ላይዘልቅ እንደሚችል ያስጠነቀቁት ምሁራን፤ አፋጣኝ የፖለቲካ ውሳኔ እንዲሰጥበት መንግሥትን ጠየቀዋል።
እንደ ኃይድሮጂኦሎጂስቱ ፕሮፌሰር ጤናዓለም አየነው ገለፃ፤በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙት ዝዋይ፣ ሻላ፣ አብያታና ላንጋኖ ሐይቆች በአንድ ወቅት አንድ ትልቅ ሐይቅ ነበሩ።
ፕሮፌሰር ጤናዓለም በሐይቁ ላይ ከ25 ዓመታት በላይ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በአብያታ ሐይቅ ላይ የሚካሄደው ሶዳ አሽ ማምረትና በዝዋይ ሐይቅ ላይ የሚካሄዱት የመስኖ እርሻ ሥራዎች፣ ወደአብያታ ሐይቅ የሚገባውን የውኃ መጠን ከጊዜ ወደጊዜ በመቀነስ ሀይቁን ወደ መደረቅ እያደረሱት እንደሆነምሁራኑ አመልክተዋል።
የአብያታ ሐይቅ ውኃ በአብያታ ሻላ ሶዳ አሽ አክሲዮን ማኅበር አማካይነት በፓምፕ እየተሳበ ለፋብሪካው አገልግሎት እንደሚውል ያስታወቁት ምሁራን፣ በየጊዜው የሐይቁ ጨዋማነት እየጨመረ መምጣትም ለሶዳ አሽ ምርት ተፈላጊ እንዲሆን ማድረጉን ይናገራሉ፡፡
በዝዋይ ሐይቅ ላይ የሚካሄደው የመስኖ እርሻን ተከትሎ የቡልቡላ ወንዝ የሚጠለፍበት ግድብ የ50 በመቶ ውኃ ገድቦ እንዲይዝ ቢደረግ፣ አብያታ ሐይቅ እርቃኑን እንደሚቀርም ምሁራኑ ይገምታሉ፡፡
የዝዋይ ሐይቅ ወደ አብያታ ሐይቅ ለሚገባው የውኃ መጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያወሱት ፕሮፌሰሩ፤ አብያታ-ከ45 በመቶ በላይ የውኃ መጠኑን ቡልቡላ ከተባለው ወንዝ ያገኝ ነበር ብለዋል፡፡
አሁን መንግሥት በወንዙ ላይ ለመስኖ ብሎ በገነባው ግድብ ምክንያት ግን- ወደ ሐይቁ ይገባ የነበረውን የውኃ መጠን በመቀነስ፤ ጫና ይፈጥራል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡
ከዚህ ባሻገር የዝዋይ ሐይቅ ለመስኖ እርሻ ሥራ እንደልብ እየዋለ በመሆኑ ሳቢያ፣ በዝዋይ ሐይቅ የሚታየው የውኃ መቀነስ፣ በአብያታ ሐይቅ ላይ የ60 በመቶ ቅናሽ የማስከተል ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ፕሮፌሰር ጤናዓለም አብራርተዋል።
የአብያታ ሐይቅ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1970ዎቹ ጀምሮ በመቀነስ ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከጂኦሎጂካልና ሌሎች ተፈጥሯዊ ተፅዕኖዎች ይልቅ፣ በሰው ሠራሽ ምክንያት በሐይቁ ላይ የሚደርሰው ጫና- የመድረቁንም፣ የመሞቱንም ሒደት እያፋጠነው በመሆኑ፣ መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ በመስጠት ሐይቁን ከጥፋት እንዲታደገው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአብያታና የሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊም የአካባቢው ነዋሪዎች የሐይቁን የወደፊት ሕልውና በማስመልከት የድረሱለት ጥሪ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጋዜጣው አመልክቷል።
በአንድ ጊዜ ከ20 እስከ 30 ሺሕ የሚደርሱና ከሰባት በላይ የፍላሚንጎ አዕዋፍት ዝርያዎችን ማየት የሚቻልበት የነበረው አብያታ ሐይቅ፣ በአሁኑ ወቅት ፍላሚንጎዎቹ እየተሰደዱ መሄዳቸው ሳያንስ በውሾች መበላት እንጀመሩም፣ የዙሎጂካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ሥዩም መንግሥቱ አስታውቀዋል፡፡ በቀድሞ ጊዜ ልዩ ልዩ የዓሳ ዝርያዎች ይገኙበት ከነበረው ከአብያታ ሐይቅ፣ በተለይ አልካላይን ቴላፒያ የተባለው ብርቅዬ የዓሳ ዝርያ ጠፍቶ እንደቀረ ም ዶክተር ሸዩም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ከአብያታ ሻላ ሶዳ አሽ ፋብሪካ ተወክለው የመጡ ግለሰብ ፋብሪካው እያደረሰ ስላለው አደጋ ማብራርያ ቢጠየቁም፤ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ ሷይሆኑ ቀርተዋል።
ምሁራኑንና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ለውይይት በመጥራት ለአሳሳቢው የአብያታ ሐይቅ ህልውና መፍትሔ እንዲፈላለግ አጋፋሪ የሆኑት በዙሎጂካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የውኃ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ፈታሂ ናቸው፡፡ ምሁራኑ ከ20 እስከ 50 ዓመታት ባሉት መጪዎቹ ጊዜያት አብያታ ሐይቅ ሞቶ ባዶ ሜዳ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ የሐይቁ የውኃ ይዘትም ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ መቀነሱን በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡ ለአንድ ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የድኅረ ምረቃ ሕንፃ ውስጥ በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ የሐይቁን ሕልውና የሚያቃነቅን የውትወታና የቅስቀሳ ቡድን እንደተቋቋመ ታውቋል፡