መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የዞን ሁለት ዋና ከተማ በሆነው አብአላ የሚኖሩ 15 ሺ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ራሳችንን በራሳችን ለማስተዳደር ልዩ ወረዳ ይሰጠን በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ አይደለም ሲሉ የአፋር ሰብአዊ መብቶች ሃለፊ አቶ ገአስ አህመድ ገልጸዋል።
አቶ ጋአስ በዱብቲ ከተማ በርካታ የአማራ፣ የኦሮሞ እና የትግራይ ተወላጆች ቢኖርም አንድም ቀን የወረዳ ጥያቄ አለማንሳታቸውን ገልጸው፣ ከመቀሌ በ45 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አብአላም ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ያቀረቡት ጥያቄ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል። የአፋር ክልል በህወሀት ሰዎች የሚመራ መሆኑን የገለጹት አቶ ገአስ፣ ተወላጆቹ ወረዳ ይሰጠን ከሚሉ ክልሉ የራሳቸው መሆኑን ቢያውቁት ይሻል ነበር ብለዋል።
አቶ ገአስ እንደሚሉት በአብላ የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ከተማዋ ሸከት ተብላ እንድትጠራ እንዲሁም የአፋር ክልላዊ መንግስት በከተማዋ መሬት ለኢንቨስትመንት መስጠት አይችልም የሚሉት ጥያቄዎች የመብት ጥያቄዎች ሳይሆኑ የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ በአፋር ክልል የህወሀት ባለስልጣናት ግምገማ እያስደረጉና የራሳቸውን ሰዎች እየሾሙ ክልሉን ለውድመት መዳረጋቸውን አቶ ገአስ አመልክተዋል
በጉዳዩ ዙሪያ የአብአላ የትግራይ ተወላጆችን ተወካይ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።