የፌደራል ፖሊስ አባላት ከግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው የጠረጠሩዋቸውን ወጣቶች ይዘው አሰሩ

ሚያዚያ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው ከአዲስ አበባ የተንቀሳቀሱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከባህርዳር በ35 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ መርአዊ ከተማ በመሄድ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አፍነው ወስደዋል።
ፖሊሶቹ ትናንት ምሽት ወደ ከተማዋ በመግባት እና የአካባቢውን ሰዎች በማስፈራራት ልጆቹን አፍነው የወሰዱዋቸው ሲሆን፣ አንድ ወጣት ክፉኛ መደብደቡን ለማረጋጥ ተችሎአል። የታሰሩት ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸውም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢህዴን ኢህአዴግ እንዲሁም በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የደህንነት ሹም በመሆን ለረጅም ጊዜ ሲያገለግል የነበረው ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ የግንቦት7 ህዝባዊ ሀይልን መቀላቀሉ ታውቋል።
ሻለቃ መሳፍንት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ስላለው የዘር ችግር፣ በብአዴን ውስጥ ስለሚነሱ ቅሬታዎች እና መሰል ጉዳዮች ዛሬ ከኢሳት ጋር ሰፊ ቃለምልልስ አድርጓል። ሙሉ ቃለምልልሱ በቅርቡ ይቀርባል።