መጋቢት ፫(ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት ለሚ እየተባለ በሚጠራው ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በኮብል ድንጋይ ማንጠፍ ስራ ላይ በተሰማሩ የደቡብ እና የኦሮሞ ተወላጅ ሰራተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቁጥሩን በትክክል ለማወቅ ባይቻልም በርካታ ሰዎች ሙትና ቁስለኛ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ኢሳት ሰዎች መገደላቸውን መረጃ የደረሰው ቢሆንም፣ አሀዙን ከመንግስት ወይም ከሌላ ገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልቻለም። ይሁን እንጅ አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገ ሰራተኛ ጸቡ እንደተነሳ፣ ሸሽቶ ለማምለጥ መቻሉን ለኢሳት ተናግሯል።
ፖሊስ ጸቡን ለመቆጣጠር ሙከራ ቢያደርግም ደም መፋሰሱን ለማስቀረት እንዳልቻለ ታውቋል። ከ10 እስከ 12 ሺ ሰራተኞች እንደሚሳተፉበት በሚነገረው በዚህ የኮብል ድንጋይ ማንጠፍ ፕሮጀክት ላይ የተነሳው ጸብ የቆየ መሆኑም ታውቋል።
የዛሬው ግጭት መነሻ ከዚህ ቀደም አንድ የደቡብ ተወላጅ አንድ የኦሮሞ ተወላጅን ሴት ልጅ በመምታቱ ነው። በዛሬው እለት የኦሮሞ ተወላጆች ተደራጅተው በመምጣት በደቡብ ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ፖሊስ ሀላፊዎችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።