በኢምግሬሽን አዲስ ፓስፓርት ለማውጣት እስከ አምስት ሺ ብር ጉቦ እየተጠየቀ ነው

የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-አገሪቱን እየለቀቀ የሚሰደደው ህዝብ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ  ህዝቡን ማስተናገድ ያልቻሉት የኢምግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ መ/ቤት አንዳንድ ሰራተኞች አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ወይም ለማሳደስ ለሚፈልጉ
ኢትዮጵያዊን ፈጣን አገልግሎት እንሰጣለን በማለት በነፍስ ወከፍ እስከ ብር 5ሺ ብር ጉቦ እየጠየቁ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት
ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

መ/ቤቱ ከጊዜ ወደ ግዜ አገልግሎት አሰጣጡ እያሽቆለቆለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተለይ ወደ መካከለኝ ምስራቅ አገራት
ለስራ የሚጓዙ በሺ የሚቆጠሩ ሴቶች ከፍተኛ መጉላላት፣ እንግልትና ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡

አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት፣ለማሳደስ፣የስም ስህተት ለማረም እና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከክልሎች ጭምር
በየቀኑ በሺ የሚቆጠሩ አግልግሎት ጠያቂዎች ወደ አዲስ አበባው ኢምግሬሽን መ/ቤት የሚጎርፉ ሲሆን፣ ጉዳያቸው ቶሎ
ሊፈጸም ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ በገንዘብ እጥረት ጎዳና ላይ ለማደር ጭምር እየተገደዱ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ምክንያት በርካታ ሴቶች የመደፈርና የዝርፊያ አደጋ የሚያጋጥማቸው መሆኑን የጠቆመው የውስጥ ምንጮች፣ መ/ቤቱ አገልግሎት
አሰጣጡን አሻሽሎ ቀልጣፋ ከማድረግ ይልቅ አንዳንድ ሰራተኞቹ በአካባቢው ካሉ ደላሎች ጋር በመሻረክ ቅድሚያ
አግልግሎት ለማግኘት ከሚፈልጉ ግለሰቦች እስከአምስት ሺ ብር የሚገመት ጉቦ በነፍስ ወከፍ እየተቀበሉ በማስተናገድ
ላይ ናቸው።

መ/ቤቱ አግልግሎት ጠያቂዎችን በከፍተኛ እንግልትና ወረፋ አልፈው ሲቀርቡ ከሶስት ወራት በላይ የረዘመ ቀጠሮ
መስጠቱ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር መክፈቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ትልቁ የአገሪቱ የደህንነት ተቋም በሙስናና ብልሹ አሰራር ውስጥ በመዘፈቁ ዜጎች ብቃት ያለው አገልግሎት አጥተው
በገዛ አገራቸው ለእንግልትና ለመከራ መዳረጋቸው እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን ምንጫችን አክሎ ገልጾአል፡፡

አንዳንድ ወገኖች አገሪቱን እየለቀቀ የሚሄደው ህዝብ መበራከት ፣ ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጣሉ። አገሪቱን እየጣለ የሚሰደደው ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም እንደ ኢምግሬሽን ባለስልጣናት መረጃ። ወደ አረብ አገራት በህጋዊ መንገድ ከሚወጣው ህዝብ ቁጥር የበለጠ በኬንያ ወደ ደቡብ አፍሪካና ወደ ሌሎች አገራት የሚሰደደው ኢትዮጵያዊ ቁጥር እንደሚበልጥ እነዚህ መረጃዎች ያሳያሉ።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚሰደደው ለስራ ፍለጋ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ስርአት መበላሸትና የተስፋ እጦት ለስደቱ ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ።