የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በስደት የሚገኙነትን አራተኛው ፓትርያርክ ጨምሮ በውጪ አገር ያሉ አባቶችን ስሕተት፣ ጥፋትና ዕርቀ ሰላሙን ማፍረስ የሚያትት እንዲሁም ፓትርያርኩ ከሥልጣን የወረዱት ተገደው ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ መሆኑን የሚያትት ባለ 52 ገጽ አነስተኛ መጽሐፍ ታትሞ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ደጀሰላም ዘግቧል።
ይኸው በአቡነ ማቲያስ ዕለተ ሲመት ጀምሮ መሰራጨት የጀመረው መጽሐፍ በብዙዎች አባባል የቤተ ክህነቱ “ጂሐዳዊ ሐረካት” የተሰኘ ሲሆን አዲስ ተሿሚው ፓትርያርክ ይቀጥላል ሲሉ ተስፋ ከሰጡት የዕርቅ ሒደት ተቃራኒ ሆኖ መገኘቱን ድረገጹ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም “ዶኩመንታሪ” ፊልም እንዲሰራበት ኮሚሽን ተከፍሎበታል በሚባለው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዕርቁን በጉጉት ይጠብቅ የነበረውን ምእመን ለማሳመን ረብጣ ብር እየፈሰሰ እንደሚገኝም አጋልጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 13 አባላት ባሉት የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ የምዕመናኑ ወኪል ተብለው ከተሰየሙ ሶስት አባቶች መካከል አንዱ፣ የካቲት 25 ቀን አቡነ ማትያስ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሩት የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ “ቅ/ሲኖዶሱ ያወጣውን ሕገ ደንብ መፈጸምና ማስፈጸም የማይችል ከኾነ ቤተ ክርስቲያን ለከፋ ፈተና እንደምትጋለጥ እሰጋለሁ። አስመራጭ ኮሚቴውም የድካሙን ያህል ውጤት አስገኝቷል ብዬ አላምንም። ከዚህ ሁሉ የመራጮች እንግልትና የገንዘብ ወጭ ይልቅ ቅዱስ ሲኖዶሱ በዝግ ስብሰባ የሚሻለውንና ወቅቱን የዋጀውን አባት መርጦ ቢሠይም ደግና የዋህ በኾነው ምዕመናን ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸው ታውቋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ የአስመራጭ ኮሚቴውን ሪፖርት ለመስማት እንኳ ያልታገሡት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ‹‹ሲኖዶሱንና ሲኖዶሱን፤ ሲኖዶሱንና ቤተ ክርስቲያንን ማእከል አድርጎ ከግለሰብ እና ከሌሎች አካላት ጫና ነጻ ኾኖ መሥራት ካልተቻለ ችግሩ ይቀጥላል፤ የከፋም እንዳይኾን ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግና እንደ አባትም መጸለይ አለብን፤›› ብለው በመናገር ስብሰባውን አቋርጠው እንደወጡ ተሰምቷል።
የ6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የምርጫ መርሃ ግብር፣ ሙሉ ለሙሉ የስርዓቱ ጣልቃ ገብነት የተንፀባረቀበትና፣ መራጮችም ድምፃቸውን ለፈቀዱት አባት በነፃነት እንዳይሰጡ የተዋከቡበት እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።
በዚሁ የፓትርያርክ ምርጫ የተካፈሉ አንድ ከምዕራብ ጎጃም ሃገረ ስብከት የመጡ ድምፅ ሰጪ፣ በአዳራሹ ከነበረው የጀርመን ድምጽ ራድዪ ወኪል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ምርጫው እገሌን ምረጡ ይሄን ምረጡ የሚባል አሰቃቂና በጣም አስቀያሚ ነገር አለው” በማለት የምርጫው ክንውን ከመነሻው ጀምሮ በፍፁም ነፃነት እንዳልተከናወነ ለመጠቆም ሞክረዋል። ዘገባውን ያጠናከረው የአውስትራሊያው ቅዱስ ሀብት በላቸው ነው።