የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ለኢሳት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ሰራዊቱ እና የሶማሊ ልዩ ምልሻ በጋራ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ የውሀ ጉድጓዶችን ተቆጣጥረው ህዝቡን ገንዘብ በማስከፈል እያሰቃዩት ነው። ድርጅቱ ለአለማቀፍ ድርጅቶች ባሰማው የድረሱልን ጥሪ ሰራዊቱ በአንድ ሰው እና በእንስሳ ቁጥር ልክ ገንዘብ እያስከፈለ ነው።
አንድ ቤተሰብ ወደ ውሀ በወሰዳቸው ግመሎች፣ ፍየሎችና በጎች ልክ ለውሀው እንደሚከፍል የገለጠው መግለጫው በአማካኝ አንድ ቤተሰብ እስከ 12 ሺ ብር በወር የመክፈል ግዴታ ጠጥሎበታል ሲል አስታውቋል።
ከፍተኛ ድርቅ በተስፋፋበት ኦጋዴን እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ በህዝቡ ላይ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት እርምጃ በመሆኑ መንግስት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ድርጅቱ ገልጿል።
በተለይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ እንዲታደግ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም። የኦጋዴን አካካቢ አሁንም ከፍተኛ የጤር ቀጠና መሆኑ ይታወቃል።