የካቲት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፓርቲዎቹ የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት ባለፈው ቅዳሜ ነው። በፊርማ ስነስርአቱ ላይ የፓርቲዎቹ ጥምረት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ ” የተፈረመው ሰነድ የመጀመሪያ የመግባቢያ ሰነድ መሆኑን ገልጠው፣ የኢህአዴግ የ21 አመታት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያን ለረሀብ፣ ለድህነት፣ ለስደት፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ለኢፍትሀዊነት፣ ለሙስና ዳርጓታል ብለዋል።
የአዲሱ ስብስብ ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው በዚህ ታሪካዊ የአድዋ ቀን ይህን የመጀመሪያ ደረጃ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረማችን ደስታ ይሰማናል ፣ የፓርቲዎቹ የጋራ ጉዞ ይቀጥላል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ ” ገዢዎቻችን ከሰጡን የአስተሳሰብ አድማስና የትግል ድንበር ወሰን ተሻግረን ልዩነቶቻችችንን በአወንታዊ ጎኑ በመጠቀም፣ አገራችንን ህዝባችን በማስቀደም ሁላችንም በእኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት ለመመስረት በትብብር ቆመን የሰው፣ ሙያ፣ እውቀትና ልምድ፣ ማቴሪያልና ፋይናንስ በማሰባሰብ ህገመንግስታዊ መብታችንን ሰላማዊ የትግል ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በጋራ እንሰራለን” ሲሉ በሰነዱ ላይ አስፍረዋል።
33ቱ ፓርቲዎች < መንግስት በሚወስዳቸው የሀገር እና የህዝብ ዘላቂ ጥቅሞችን በሚጎዱ እርምጃዎች ላይ ተወያይቶ የጋራ አቋም ለመያዝ፣ ገዢው ፓርቲ ህገወጥ እርምጃ በሚወስደበት ጊዜ ሁሉም ፓርቲዎች እርምጃውን እንዲቃወሙ፣ ምርጫውን በተመለከተ የጋራ ስልት መቀየስ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተግቶ መስራት፣ በጋራ የፋይናንስ ድጋፍ ማሰባሰብ፣ በተቃዋሚዎች ላይ የሚሰነዘሩ የማጥላላት፣ የማንኳሰስና የመከፋፈል አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ማውገዝ” የሚሉትን በጋራ ለማከናወን ተስማምተዋል።
33ቱ ፓርቲዎች አብረው ለመስራት ስምምነት ላይ የደረሱት፣ በ2005 የሚደረገውን የአዲስ አበባና አካባቢ እንዲሁም የወረዳዎች ምርጫ አፈጻጸም ከተቃወሙ በሁዋላ ነው።