የካቲት ፩፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሶሶት አመት በፊት የነደፉት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ሊጠናቀቅ ሁለት አመታት ብቻ የቀሩት ቢሆንም፣ በቀሪዎቹ አመታት ውስጥ ዋና ዋና የሚባሉትን ፕሮጀክቶች ለፍሬ ለማብቃት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አጋጥሟል።
የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት መንግስት በስሜት ላይ ተመስርቶ የነደፈውን እቅድ መልሶ እንዲከልሰው ግፊት በማድረግ ላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ አይነቱን እርምጃ ለመውሰድ እስካሁን ፈቃደኛ አልሆነም።
ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚባሉትን የአባይ ግድብ ግንባታ፣ የባቡር ሀዲድ ዝርጋታና የስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ ለማከናወን መንግስት ከውጭ አገር መንግስታት በብድር መልክ ለማግኘት የነደፈው እቅድም ሆነ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመሰብሰብ ያቀደው እቅድ በተፈለገው መልኩ አልተሳካም።
ኢትዮጵያውያን የአባይን ግድብ ግንባታ አብዛኛውን ወጪ ይሸፍናሉ ብሎ መንግስት ተስፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ተስፋው ግን ከተስፋነት አለመዝለሉን መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተረዳው ጉዳይ ሆኗል ሲል ዘጋቢያችን ገልጿል።
በመላው አገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ያለፍላጎታቸው በሚቆረጥባቸው ገንዘብ ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ እያሰሙ መሆኑ መንግስት ህብረተሰቡን አስገድዶ ገንዘብ በማስከፈል ወይም ፕሮጀክቶችን በመሰረዝ መሀል አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል። ህብረተሰቡ የሚያሰማው ተቃውሞ እያየለ መምጣት መንግስት አስገድዶ ቦንድ የማስገዛቱን እርምጃ እንዲቀንስ አድርጎታል።
ተዋቂው ባለሀብት ሼክ ሁሴን አላሙዲንን ጨምሮ ታዋቂ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ቃል የገቡት ገንዘብ መጠን አነስተኛ መሆን፣ ከዚያም አልፎ ቃል የገቡትን እንኳ በውቅቱ ለማስገባት ማመንታታቸው ለመንግስትም ጭምር እንቆቅልሽ እንደሆነበት ዘጋቢያችን ገልጿል።
ከሁሉም በላይ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ማሰሪያ ያዋጡት ገንዘብ እጅግ አነስተኛ መሆን፣ መንግስት በውጭ የሚኖሩ የኢህአዴግ አባላት እንኳ ለማዋጣት ፈቃደኛ አልሆኑም የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል።
ባለፈው የበጀት አመት ወደ ውጭ የተላከው ምርት አነስተኛ መሆንና ከሽያጩም የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ማነስ ለገንዘብ እጥረቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን በአገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጦች ሲዘግቡት ቆይተዋል።
መንግስት የአምስት አመቱ እቅድ ሊሳካ የማይችል መሆኑን በይፋ ለመናገር ጊዜው አሁን አይደለም የሚል አቋም ቢይዝም ውሎ አድሮ ይህን ከማለት እንደማያመልጥ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የአምስት አመቱ የእድገት እና የትራንስርሜሽን እቅድ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የተነደፈ መሆኑን እቅዱ በወጣበት አመት መናገራቸው ይታወሳል።