ስድስተኛ ፓትርያር ለመሾም የሚደረገውን ጥድፊያ አጥብቀው እንደሚቃወሙ በኒውዮርክና አካባቢው የሚገኙ የ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን አስታወቁ

የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-ምዕመናኑ ባወጡት መግለጫ  ስድስተኛ ፓትርያርክ ለማስቀመጥ በአገር ቤት እየተደረገ ያለውን ጥድፊያ እንደሚቃሙትና በውጪ የሚገኘው ሲኖዶስ በጉዳዩ ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ እንደተቀበሉት ገልጸዋል።

ይህን ያደረጉትም አንዱን ወገን አግልለው አንዱን ወገን ለመደገፍ ሳይሆን መጽሐፍ ፦<<እውነትን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው>>ባለው መሰረት ከሁለቱም ወገን የተባሉትን እና እየሆነ ያለውን ነገር ከሥረ-መሰረቱ በመመርመር እንደሆነ አስረድተዋል።

<<በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው በደል ያስከተለው ሀዘንና ጉዳት በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም>> የሚለው የምዕመናኑ መግለጫ፤ የቤተ
ክርስቲያኑ ካህናትና ምዕመናን ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ዕርቀ ሰላም እንዲወርድና ሕገ ቤተክርስቲያን እንዲከበር ሲመኙና ሲጸልዩ እንደኖሩ ያወሳል።

 

ከዚህም ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱ የቁርጥ ቀን ልጆች፦<< የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው>> በሚለው አማናዊ ቃል መሰረት የሰላምና የአንድነት ጉባኤ በማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ባሉት አባቶች መካከል ዕርቅ እንዲፈጠርና ቀኖና ቤተክርስቲያንም እንዲከበር ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን ያወሳው መግለጫው፤ይህም በጎ ተግባራቸው  ሲያስመሰግናቸው ይኖራል ብሏል።

 

ይሁንና  የመጨረሻው ድርድር ፍፃሜ ሳያገኝ ከአዲስ አበባው ሲኖዶስ የተሰማው ድምፅ ካህናቱንና ምዕመናኑን ከበፊቱ ለከፋ ሀዘን ዳርጎታል ያሉት የኒውዮርክ ምዕመናን፤ይህንም ተከትሎ ከህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሰፊ መግለጫ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

<<እኛም በኒውዮርክና በአካባቢው የምንገኝ ምዕመናን ከሁለቱም ወገን የተሰጡትን መግለጫዎች በጥልቅ በመመርመር እውነትን <የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው> ተብሎ እንደተጻፈ በውጭ ሀገር በሚገኘው ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠውን መግለጫ ሙሉ በሙሉ በመደገፍና በውስጡም የተሰጡትን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል ቆርጠን ተነሥተናል>> ሲሉም አቋማቸውን አሳውቀዋል።

ምዕመናኑ ይፋ ባደረጉት ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ ላይ

 

<<ባለፉት 21 ዓመታት ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ በመሾሙ ሳቢያ ያስከተለውን ጥፋት በማረምና በማስተካከል፣ የተፈጠረውንም ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅሞ ህጋዊውን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስን ከነሙሉ ክብራቸው ወደ መንበራቸው በመመለስ ፋንታ፤ በጥፋት ላይ ጥፋት እንዲሉ ሌላ ስድስተኛ ፓትርያርክ ለመሰየም የሚደረገውን ጥድፊያ እንቃወማለን፣ ተመራጩንም አንቀበልም።>>ብለዋል።

የተለያዩ መንፈሳዊ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት፣ ማኅበረ ምዕመናኑ ስለቅዱስ ሲኖዶስ አመሠራረትና ስለ ቀኖና ቤተክርስቲያን መከበር አሰፈላጊነት ጥርት ባለ መንገድ እንዲገነዘብ በማድረግ፤ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላም፤ ለቤተክርስቲያናችን ፍቅርና አንድነት በሙሉ ልብና በሙሉ ኃይል እንዲነሳ ያለሰለሰ ጥረት እናደርጋለን።ብለዋልም-የኒውዮርክ ምዕመናን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው የመከፋፈል አደጋ የኢትዮጵያና የውጪ በሚል ብቻ እንዳላበቃና  <<ከሁለቱም ያልወገነ ገለልተኛ>> በሚል ስም የሚጠራ ሦስተኛ አካል እንዳለ የጠቆመው መግለጫው፤<< ቅድስት ቤተክርስቲያናችን አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት በአሁኑ ወቅት ሰላምና አንድነትን ዕውን ለማድረግ እርምጃ መውሰድ የግድ ይላል።>>ብሏል።

ስለዚህም በሰላምና አንድነት ኮሚቴ አማካይነት በህጋዊው ሲኖዶስና በገለልተኛው ወገን መሀከል አንድነት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ የዕርቅ ድርድሩ በአስቸኳይ እንዲጀምር ጠይቋል።

በመጨረሻም በህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከምን ጊዜውም በበለጠ የቅዱስ ሲኖዶሱን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል የሚፋጠን ልዩ ኮሚቴ እንዲቋቋም መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን፣ ያለው መግለጫው፤ በዚሁም መሠረት በኒውዮርክና በአካባቢው ቤተክርስቲያናት ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን መጀመሩን አስታውቋል።