በብራሰልስ የሚካሄደው የኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ቅድመ ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ዘጋጆች ገለጹ

የካቲት ፩፮ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እውቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አርቲስት ታማኝ በየነ የሚሳተፍበት በቤልጂየም ብራሰልስ የኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ሲካሄድ መሰንበቱን የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ገበየሁ ደስታ  ለኢሳት ገልጸዋል።

በቤልጂየም የኢትዮጵያውያን ኮሚቴ ማህበር ከኢሳት የቀረበለትን የትብብር ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ እንዳሳዘናቸው  አቶ ገበየሁ አልሸሸጉም ።

የኢሳት የገቢ መሳባሰቢያ አዘጋጆች ለማህበሩ ያቀረቡት ጥያቄ ፣ የኮሚኒቲውን ኔት ወርክ በመጠቀም ጥሪውን እንዲያስተላልፉላቸው የሚጠይቅ ነበር።

ጉዳዩን በማስመልከት በቤልጂየም የኢትዮጵያ ማህበር ሊቀመንበር ለሆኑት ለአቶ ያሬድ ሀይለማርያም እና ለዋና ጸሀፊው ለጀርመን ድምጽ ዘጋቢው አቶ ገበያው ንጉሴ ጥያቄ ብናቀርብም፣ መሪዎቹ በጽሁፍ ካልሆነ በስተቀር በቃል መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

የኮሚቴው መሪዎች የኢሳትን ጥያቄ ለመቀበል ያልፈቀዱት ኢሳት ገለልተኛ ሚዲያ ነው ብለው ባለማመናቸው መሆኑን ተናግረዋል። ኢሳት ከተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘርበትን ትችት በአግባቡ ባለማስተባባሉ እንዲህ አይነት አመለካከት ለመያዝ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቱን የጠየቅነው ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም፣ ሊ/መንበሩ  አቶ ያሬድ ሀይለማርያም በተደጋጋሚ በኢሳት ላይ ቀርበው ቃለምልልስ መስጠታቸውን አስታውሶ፣ “ቃለ ምልልስ ሲሰጡ የኢሳት ገለልተኝነት ጥያቄ አልታያቸውም ነበር፣ ዛሬ  እርዳታ ስንጠይቃቸው ግን የገለልተኝነት ጥያቄ አነሱ፣  ለማንኛውም  ግለሰቦች የመሰላቸውን አመለካከት መያዝ ይችላሉ፣ መንግስትም አሸባሪ ማለቱን መርሳት የለብንም ” ብሎአል።

ጋዜጠኛ ፋሲል  “ኢሳት ገለልተኛ ሚዲያ ነኝ የሚለው  ከእምነት ተነስቶ   እንጅ  ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ አለመሆኑን ገልጾ፣ አላፊ አግዳሚው ለሚያናፍሰው አሉባልታ ኢሳት መልስ ለመስጠት ጊዜውም ፍላጎቱም የለውም፤ ጊዜው ተረት ተረት የምናወራበት ሳይሆን፣ ታሪክ የምንሰራበት ነው”  ሲል ተናግሯል።

የቤልጂየም የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ነገ እሁድ ፌብሩዋሪ 24፣ 2013 ይካሄዳል።