ሰመጉ የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም የተከሰሱ ሰዎችን ሕገመንግስታዊ መብት የጣሰ ነው ባወጣው መግለጫ አስታወቀ

የካቲት ፩፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰመጉ በዚሁ መግለጫው በፌዴራል ፖሊስና በብሄራዊ ደህንነት እና ጸጥታ ባለስልጣን ተዘጋጅቶ በኢቲቪ እንዲቀርብ የተደረገው ፊልም ተጠርጣሪዎቹ በሕገመንግስቱ መሰረት በተከሰሱበት ወንጀል ከፍርድ በፊት እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብታቸውን የጣሰ መሆኑን ጠቁሞ ይህ በመሆኑም ከአሁን በኋላ ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤት የመከላከያ ምስክሮችን የማቅረብ አቅማቸው አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሶአል፡፡

የፌደራል ፖሊስ እና የብሄራዊ ደህንነት እና ጸጥታ ባለስልጣን እንደ ህገመንግስት ተቋምነታቸው በአሁኑ ሰአት በፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ማእከል አቃቢ ህግ በነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ በከፈተው የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ በምርምራ ያገኙትን ማስረጃ እንደሚያቀርቡ ቢጠበቅም፣ ተቛማቱ በህገመንግስቱ አንቀጽ 20 የተደነገገውን ዜጎች ፈርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብታቸውን በመጣስ ፣ ተከሳሾች ወንጀል ስለመፈጸማቸው አውጅዋል ሲል አስታውሷል።

ዘጋቢ ፊልሙ ፍርድ ቤቶች በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት የሚያዛባ ይሆናል ያለው ሰመጉ፣ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በመንግስት በኩል የተወሰደውን ድርጊት ከማውገዝ ባተጨማሪ ዘጋቢ ፊልሙን ያዘጋጁት እና እንዲሰራጭ ያደረገው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ድርጅት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የሚመለከተው የመንግስት አካልም ድርጊቱን በማውገዝ አስፈላጊውን ማስተካከያ  እንዲያደርግ ጠይቋል።