የኢህአዴግ አጃቢ ፓርቲዎች ከምርጫው ሊወጡ ይችላሉ ተባለ

የካቲት ፩፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ አጋር እንደሆኑ የሚነገርላቸውና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ እየተባለ በሚጠራው ተሳታፊ የሆኑ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ፓርቲዎች ለመጪው ምርጫ፤ በምርጫ ቦርድ በኩል የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ በአጃቢነት ከገቡበት ምርጫ ተገፍተው ሊወጡ እንደሚችሉ ተጠቆመ፡፡

ቀደም ሲል በአቶ ልደቱ አያሌው ይመራ የነበረው ኢዴፓ፣ በአቶ አየለ ጫሚሶ ሊቀመንበርነት የሚመራው ቅንጅት፣መኢብን ፣ራዕይ ፣ኢፍዴሃግ እና ሌሎችም እምብዛም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ የሌላቸው ፓርቲዎች የተሰባሰቡበትና ኢህአዴግም እንደ አንድ ፓርቲ እየተሳተፈበት ባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ላይ ለመጪው
ምርጫ  በሚሊየን የሚቆጠሩ ዕጩዎችን ማቅረብ የግድ በመሆኑ ለዚህ ከፍተኛ ስራ ደግሞ ፓርቲዎች የገንዘብ አቅም እንደሌላቸው ታሳቢ ተደርጎ በምርጫ ቦርድ በኩል የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ኢህአዴግ ግፊት እንዲያደርግላቸው ከአንድ ወር በፊት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

በዚህ ምክንያት ፓርቲዎቹ አንዳንዶቹ ለይስሙላ በጥቂት ቦታዎች ለመወዳደር ዕጩ ማቅረባቸው ቢረጋገጥም በተግባር በገንዘብ ችግር ለመሳተፍ የሚችሉ ባለመሆናቸው
ኢህአዴግ ያለአንዳች አጃቢ ፓርቲ የዘንድሮውን ምርጫ ብቻውን ተወዳድሮ እንደሚያሸንፍ ከወዲሁ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በየዓመቱ ከኢህአዴግ የአንድ ሚሊየን ብር የበጀት ድጎማ ከሚደረግላቸው ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል ኢዴፓ የሚባለው ፓርቲ የፋይናንስ ድጋፉ መከልከሉ ከተረጋገጠ በኋላ ባለፈው ሳምንት ከምርጫ ሙሉ በሙሉ ላለመውጣት ሲል ብቻ በአንድ ዕጩ እንደሚወዳደር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ሌሎቹ ፓርቲዎችም ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ስላለባቸው በምርጫው የመሳተፋቸው ነገር እስካሁን የተረጋገጠ አለመሆኑን ምንጫችን ጠቅሶአል፡፡

በአገሪቱ ተመዝግበው ይንቀሳቀሳሉ ከሚባሉ ከ65 በላይ ፓርቲዎች ውስጥ 28 ገደማ የሚሆኑት ከምርጫ በፊት ውይይት እንዲቀድም ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ  ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው የሚታወቅ ሲሆን በኢህአዴግ
አባላትና ደጋፊዎች የተሞላው ምርጫ ቦርድ ግን 15 ገደማ ፓርቲዎች በተወዳዳሪነት ተመዘግበውልኛል እያለ ነው፡፡