የካቲት ፩፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዘጋቢያችን እንደገለጠው በትናንትናው እለት በፈረንሳይ አካባቢ የሚኖሩ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት በድንገት ቤታቸው እየተበረበረ ቁራን ፣ የተለያዩ ሲዲዎች እና ሀይማኖታዊ መጽሀፎች ወስደውባቸዋል ።
የኢህአዴግ ካድሬዎች እና የደህንነት ሰዎች ናቸው የሙስሊሞችን ቤት እንዲፈተሽ የሚጠቁሙት ያሉን አንድ የአካካቢው ነዋሪ ፣ ፈታሽ ፖሊሶች ምንም አይነት የፍርድ ቤት ትእዛዝ ወረቀት አለመያዛቸውንም ተናግረዋል።
የፖሊሶቹ ዋና አላማ ሙስሊሞች በስነልቦና ፈርተውና ተሸብረው ነገ አርብ ከጸሎት በሁዋላ የሚያካሂደውን ተቃውሞ እንዳያደርጉ ለማድረግ ነው ሲል ዘጋቢያችን ገልጾአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል ፖሊስ አባላት የደሴ ወጣት ሙስሊሞችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደበድቡ የሚያሳይ ፊልም ኢሳት ደርሶታል። በፊልሙ የፌደራል ፖሊሶች ህዝቡን እያባረሩ ሲደበድቡ የሚያሳይ ሲሆን፣ በተለይ በአንድ ወጣት ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ድብደባ የፖሊስ አባላቱን የጭካኔ ደረጃ በደንብ የሚያሳይ ነው።
መንግስት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ የሚያደርሰው ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።