ጥር ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ኢትዮጵያ ቤንች ማጂ ዞን በጉርዳፈርዳ ወረዳ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው የሰብአዊ መብት ረገጣ መቀጠሉ ተገለጸ።
በወረዳው ባለፈው ታህሳስ አንዲት የ8 ልጆች እናት በጥይት ሲገደሉ፣ ሁለት ህጻናት በመስተዳድሩ መኪና ተገጭተው መሞታቸውን የመኢአድ ም/ሊ/መንበር አቶ ወንድማገኝ ደነቀ ለኢሳት ገልጸዋል።
ታህሳስ 28/ 2005 ከምሽቱ 4 ሰአት ሲሆን 5 መሳሪያ የታጠቁ ወተዳሮች የ8 ልጆች እናት የሆኑትን ወ/ሮ አይቼሽ ስጦታውን በመኖሪያ ቤታቸው እንደገደሉዋቸው ነው ም/ ሊቀመንበሩ የተናገሩት።
ጥር 15 ቀን 2005 ዓ/ም ደግሞ የ4 እና የ7 አመት ህጻናት በመስተዳድሩ መኪና ተገጭተው ህይወታቸው ማለፉን ከአቶ ወንድማገኝ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሎአል።
ሌሎች 23 የአማራ ተወላጆች በወህኒ ቤት በመሰቃየት ላይ መሆናቸውንም_ የመኢአድ ተቀዳሚ የፐም/ል ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማናገር ብንሞክርም አልተሳካልንም።