ሞተዋል ተብለውት የተገነዙትና የተለቀሰላቸው አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት የቀብራቸው እለት ህይወት መዝራታቸው ተገለጠ

ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሞተዋል ተብለውት የተገነዙትና የተለቀሰላቸው አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት የቀብራቸው እለት ህይወት መዝራታቸው ተገለጠ::

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው ድርጊቱ የተፈጸመው በትግራይ መቀሌ ሲሆን ከመቃብር ተርፈው ህይወት የዘሩት እናት ወ/ሮ ወይኒ ጸጋዬ እንደሚባሉ ተዘግቦል::

በመቀሌ ከተማ 03 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ወይኒ ጸጋዬ ጥቅምት 5 ቀን 2005 ማለዳ ላይ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿ አስከሬናቸው ታጥቦና ተገንዞ ቤተሰብ እያለቀሰ የቀብራቸውን ሰአት ሲጠባበቅ ከልጃቸው አንዱ ከፍተኛ ጩኅት ያሰማል፣ የጩኅቱ መንስኤ አስከሬኑ ሲንቀሳቀስ በማየቱ የተከተለ ድንጋጤ ሲሆን ለቀስተኛው አስከሬኑን ከቦ ሁኔታውን ሲከታተል መንቀጥቀጡ ይጨምራል፣ በሰሌን ተጠቅልሎና በጥብቅ ታስሮ የነበረው አስከሬን ሀኪም ባለበት ሲፈታ ወ/ሮ ወይኒ በከፍተኛ ሁኔታ መተንፈሳቸውን የአይን ምስክሮች ተናግረዋል::

ከዚህ በሆላ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት ወ/ሮ ጉሉኮስ ተሰክቶላቸው ጤናቸው በመመለሱ በቅርቡ ወደቤታቸው እንደሚመለሱ ሀኪሙ ዶክተር ዘካሪያስ ገሰሰ ለአዲስ አድማስ ገልጠዋል::

ሀኪሙ ጨምረው እንደተናገሩት ” አንድ ሰው ሞተ ተብሎ ማረጋገጥ የሚችለው በህክምና በመሆኑ ይህ ቢለመድ ከነህይወታቸው የሚቀበሩ ሰዎችን መታደግ ይቻላል ብለዋል::