ጥር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ የተደነገጉትን አንቀጾችና የእምነት ነጻነቶችን በመታስ ባለፈው አንድ አመት በእስልምና እመነት ተከታዮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ችግር ፈጥሯል ብሎአል።
ፓርቲው አያይዞም የኢህአዴግ መንግስት የሙስሊሞች ተቃውሞ ከሽብር ጋር ይያያዛል በማለት ቢገልጽም እስካሁን በታየው እንቅስቃሴ ጉዳዩ ከሽብር ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የሚታይ ምንም ነገር የለም ብሎአል። ከዚያ ይልቅ በሚያስደንቅና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረቡን ፓርቲው ለመገንዘብ መቻሉን ገልጿል።
ሰማያዊ ፓርቲ በመቀጠልም ” ኢህአዴግ ጥያቄዎችን ያነሱት ጥቂት የስልጣን ጥም ያላቸው ግለሰቦች ናቸው ቢልም ባለፈው አንድ አመት ከተደረገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እጅግ ብዙ የእምነቱ ተከታዮች በኢህአዴግ ጣልቃ ገብነት ቅሬታቸው እንደገለጡ” ተረድቻለሁ ብሎአል።
የሙስሊም አመራሮችን በተመለከተም የታሰሩት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በመንግስት እውቅና ተሰጥቷቸው ለችግሮች መፍትሄ ለማግኘት ተደጋጋሚ ውይይት ከመንግስት አካላት ማድረጋቸውን በማስታወስ፣ መሪዎቹ በተነሱት ነጥቦች ባለመግባባታቸው እና የደረሱበትን ለወከላቸው የእምነቱ ተከታዮች በማቅረባቸውና በአብዛኛው የእምነቱ ተካታዮች ዘንድ አመኔታ በማግኘታቸው ብቻ መታሰራቸው በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ቁጣ እያስከተለ መሆኑን ፓርቲው መገንዘቡን ገልጿል።
ሰማያዊ ፓርቲ “የኢህአዴግ መንግስት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚያደርገው የመብት አፈና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ተቃውሞውም በዚያው ልክ እየጨመራና ቅርጽ እየያዘ መምጣቱን” በማስታወስ፣ ኢህአዴግ በሀይማኖት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም፣ የታሰሩትም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ እንዲሁም ለጠፋው የሰው ህይወት ምክንያቱ እንዲጣራና ጥፋተኞች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።