የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ባለው የስኳር ፕሮጀክት ዙሪያ ቅሬታቸውን ገለጹ

ጥር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት የአካባቢው ምንጮች እንደገለጡት ታህሳስ 4 ቀን 2005 ዓም አቶ አባይ ጸሐየ ወደ አካባቢው በመሄድ ነዋሪዎችን ማነጋገራቸውን ተከትሎ ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ ደስታቸውን እንደገለጡ ተደርጎ በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን የቀረበው ትክክል አይደለም።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የጅንካ ከተማ ነዋሪ እንደገለጡት “አቶ አባይ ጸሀየ ነዋሪዎች ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ የተገባላቸው ቃል ባለመከበሩ ተቃውሞ አስነስተዋል በሚል ምክንያት” ወደ አካባቢው በመሄድ ህዝቡን ቢያነጋግሩም ፣ በስብሰባው ወቅት የኢህአዴግ አባላት ብቻ ተመርጠው አስተያየት እንዲሰጡ በመደረጉ ህዝቡ ቅሬታውን በይፋ እንዳይገለጥ ተደርጓል።” የአካባቢው ነዋሪዎች ቃል የተገባላቸው ግንባታዎች እንደተሟሉላቸው ተደርጎ በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን የቀረበው ዘገባ ህዝቡን ማስቆጣቱን ነዋሪው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳባቸውን የጠየቅናቸው የደቡብ ኦሞ የአንድነት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ስለሺ ጌታቸው ” መንግስት የህዝቡን ችግር አድበስብሶ ለማለፍ ሙከራ ማድረጉን ይሁን እንጅ ችግሩ ተመልሶ መምጣቱን” ገልጸዋል።

ከወራት በፊት የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ በማሰማታቸው 13 ወጣቶች ታስረው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። ወጣቶቹ ከ20 ቀናት በሁዋላ በዋስ ከእስር እንደሚለቀቁ ለማወቅ ተችሎአል።

በአካባቢው ከሚደረገው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በቦዲዎች እና በመንግስት መካከል ግጭት ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል። ችግሩ አሁንም ድረስ አለመፈታቱ ታውቋል።

በተመሳሳይ ዜናም በዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚደረገውን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ጋር ይቃወማሉ የተባሉ 4 መኖከሳት ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል።

አባ ገ/ ሕይወት ጉራጌ፣ አባ ኃይለማርያም ፣ አባ ገብርኤልና ባህታዊ ታዲዎስን የተባሉት መነኮሳት መታሰራቸውን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባህታዊ ተናግረዋል። ባህታዊያኑ በማይጸብሪ እስር ቤት ውስጥ መታሰራቸውን ባህታዊው ገልጸዋል። መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት የለም።